Saturday, February 28, 2026

 

 



 

 

ኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት እንድታቋቁም የሚያስገድዱ

9 ወሳኝ ጉዳዮች !    

 

                                                                                                

 

አካታች የሽግግር መንግስት





ምርጫ 







                                                                    ገለታው ዘለቀ

                                                                                          የካቲት 2026                                 

 

 

እንደ መግቢያ 

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ   የዚህ የሰባተኛው ሃገራዊ ምርጫ ዝግጅት ጉዳይ ነው። የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ዛሬ ኢትዮጵያ በምትገኝበት ወሳኝ የታሪክ መታጠፊያ ላይ  ምርጫ ለኢትዮጵያ ተስፋ ሳይሆን ስጋቶችን የያዘ በመሆኑ፣ ከትርጉም የለሽ ምርጫ ይልቅ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሽግግር መንግስት ማቋቋም ነው የሚለውን ሃሳብ ጠንካራ በሆኑ አምክህኖቶች መሞገት ነው። ከዚህ ሙግት ባለፈ የሽግግር መንግስቱ ቅርጽና ይዘት ላይ ትንታኔ አይሰጥም። ወደፊት በሌሎች ጽሁፎች ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ እንመለስበት ይሆናል። በዚህ ክፍል ውስጥ ወደ ሽግግር የሚገፉንን ስምንት ጉልህ ጉዳዮች ብቻ እናነሳለን። በነዚህ የመወያያ ነጥቦች ላይ የበሰለ ውይይት እያደረግን ሃገራችን ወደ ሰላማዊ ሽግግር እንድታመራ ግፊት እናድርግ።

 

                                   መልካም ንባብ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

  በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያን ወደ ሽግግር መንግስት የሚገፉን ዘጠኝ ነጥቦች

 

1.    የፓርቲዎች ቁመና

 

የፖለቲካ ፓርቲ ሌላኛው ስሙ እጩ መንግስት ሊባል ይችላል። ወደ ስልጣን ሲመጣ ደግሞ ገዢ ፓርቲ እንለዋለን። አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ መድብለ ፓርቲ ዘረጋ የበሰለ ፖለቲካ ውስጥ ገብቷል፣ ምርጫ ተስፋው ሆኗል የሚባለው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ እጩ መንግስታትን አሳድጎ አጎልብቶ ትከሻቸውን አስፍቶ ሲያበቃ ነው። የሃገሮች የምርጫ ጥራት አንድም በዚህ ሊለካ ይችላል። ምርጫ የሚባለው ግዙፍ የህዝብ መብት ፍሬ የሚያፈራውና የዴሞክራሲ ባህል የሚዳብረው በዚህ ረገድ የተሳካ ሥራ ከተሰራ  ነው። ፓርቲዎች በጣም ደካማዎች ከሆኑና ድርጅታዊና ርዕዮተ ዓለማዊ አድማሳቸው የሰፋ ካልሆነ የምርጫ እሴቱን እና ለዛውን ሁሉ ዋጋ ያሳጣዋል። እንዴውም አንዳንድ ጊዜ ከጥቅሙ ሁሉ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል።

 

በዚህ ረገድ የሃገራችንን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁመና መመዘን በተለይ በዚህ ሰዓት ምርጫ ለማድረግ እና ላለማድረግ እንደ አንድ ዋና መመዘኛ ሆኖ የሚቀርብ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መረጃ 24  የሚሆኑ ብሄራዊ ፓርቲዎችና 45 የሚሆኑ አካባቢያዊ ፓርቲዎች አሉ። እነዚህን ፓርቲዎች በተናጠል ሁሉንም ማየት ባንችልም ገዢውን ፓርቲና አንዳንድ ዋና ዋና የሚባሉትን ተቃዋሚዎችን ጠቅለል አድርገን ድርጅታዊ ቁመናዎቻቸውንና ርዕዮታቸውን እንዲሁም ህዝባዊ ቅቡልነታቸውን መገምገም ይገባናል።  እስቲ በመጀመሪያ ከብልጽግና እንጀምር።

   

የብልጽግናን ውልደትና እድገት ስንመለከት  ይህ ፓርቲ ኢህአዴግ የነበረ ሲሆን በዚያ ህይወቱ ውስጥ በስነ ምግባር ችግር እንዲሁም በአመራር ችግር ከዚያም አልፎ በጎጠኛ ፖለቲካ አራማጅነት ሲከሰስ የነበረ፣ ባደረሰው ከባድ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነት እንደ ራሱ ጥላ የሚከተለው ፓርቲ ሲሆን ይህ ፓርቲ የቄሮ፣ የፋኖ እና ሌሎች የወጣት አደረጃጀት ሰላማዊ ትግሎችን ተከትሎ ከባድ የህልውና ችግር ውስጥ ገባ።  በነዚህ ከባድ የፈተና ወራት ውስጥ እያደር ድርጅታዊ መዋቅሩ መፈረካከስ ጀመረ። ከአባል ድርጅቶቹ መካከል ህወሃት ጨርሶ አፈነገጠ።  ሌሎቹ ለጊዜው ያስታረቃቸው ነገር የህወሃት ገለል ማለት ብቻ ነበር። ከዚህ ያለፈ የተማረኩበት የለውጥ ፍኖተ ካርታ አልነበራቸውም። ህወሃትን ጥሎ የተረፈው ኢህአዴግ ወደ አዲስ ፓርቲነት ለመቀየር ብዙ ጊዜ እቤቱ ቁጭ ብሎ ራሱን ለማጥናት አልፈለገም። ከፍተኛ የስልጣን ጥማት ስላለበት እዚያው ሃገርና ህዝብ ትከሻ ላይ እንዳለ አዲስ ርዕዮት እያጠናሁ ነው፣ መደመር ይባላል፣ አዲስ ድርጅት ፈጠርኩ ብልጽግና ይባላል እያለ ራሱን የይድረስ ይድረስ ጠፍጥፎ ሰርቶ ፓርቲ ሆኖ ለመታየት ሩጫ ላይ ቆየ።  አንድ ፓርቲ አዲስ ርዕዮት ለመከተል፣ አዲስ አደረጃጀት ለመቅረጽ በአጠቃላይ እንደገና በፖለቲካ ለመወለድ ከህዝብ ስልጣን መራቅ ነበረበት ምክንያቱም ይህ ዓይነት የአስተሰሰብና የድርጅታዊ ለውጥ ሂደት የሚፈጥረው ግጭት የሃገር ግጭት እንዳይሆን። አንድ ፓርቲ ሪፎርም ሲያደርግ የለውጥ ፍትጊያ ይገጥመዋል። ለውጥ በተፈጥሮው መጓተትና ግጭት (resistance) አለው።  ለውጡን የሚታገሉ ሃይሎች ይኖራሉ። ይሄ በለውጥ ንድፈ አሳብ ውስጥ ያለ ክስተት ነው። አንድ ለውጥ ሲመጣ ኢነርሽያ ይኖራል። ኢነርሽያ ማለት ለውጡን በተቃራኒው መግፋት ማለት ነው። በመኪና ውስጥ ስንሂኤድ መኪናው ፍጥነቱን ሲጨምር ወደ ኋላ እንታገላለን። ከአዲሱ ለውጥ ጋር የተወሰነ ግፊያ ይኖራል። ይህ ጽንሰሃሳብ ነው የለውጥ ኢነርሽያ የሚባለው። ስለዚህ በለውጥ ውስጥ ግጭት የሚጠበቅ ስለሚሆን ፓርቲዎች ሪፎርም የሚያደርጉት፣ ራሳቸውን አዲስ ርዕዮት የሚያተምሩት ስልታን ላይ ሆነው የመንግስትን ማሽነሪዎች እየነዱ መሆን የለበትም።

 

ምክር የማይሰማው ኢህአዴግ ህወሃትን ቀንሶ በመደመር ባቡር ውስጥ ጉዞ ጀምረናል ሲል በዚህ መሃል ግጭት መኖሩ አልቀረም።  ከህወሃት ጋር ከባድ ቅራኔ ተፈጠረ። ከፍ ሲል እንደገለጽነው ፓርቲው ህዝብ ጫንቃ ላይ ባይሆን ኖሮ እነዚህ ግጭቶች ተቋማዊ ይዘት ኖራቸው ወደ ህዝብ ባልወረዱ ነበር። ነገር ግን ብልጽግና በድፍረትና ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ስልጣን ላይ እያለ ወደዚህ ፓርቲ አቅልጦ አዲስ ፓርቲ የመስራት ሂደት ውስጥ ሲገባ በህወሃትና በሌሎቹ መካከል የነበረው ግጭት ሃገራዊ መልክ ያዘ። በዚሁ አዲስ ፓርቲ በማዋለዱ ሂደት ውስጥ የውስጥ ቅራኔ ተፈጥሮ ቲም ለማ ፈረሰ። የፓርቲው ቀውስ ተባባሰ። ተቋማት ሁሉ የፓርቲውን ኪሳራዎች ለመሸፈን መሳሪያ ሆኑና ከባድ ችግር ውስጥ ገባን።  ፓርቲው ስልጣን ላይ እያለ ይህንን በማድረጉ የፓርቲው ግጭቶች የሃገር ግጭቶችን አመረተ። በፓርቲው መስራች አባላት መካከል የተደረገው ግጭት ብሄር ከብሄር አፋጀ። የርስ በርስ ጦርነቱ ብዙዎችን አፈናቀለ። ይህ ፓርቲ በሂደት ከችግር የማይማር በመሆኑና እያደር በከፍተኛ የፖለቲካ ኪሳራ ውስጥ በመግባቱ እነሆ ከትግራይ ለጥቆ ከአማራ ጋር ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ ገባ። ኢህአዴግ ሄዶ የተሻለ ስርዓት ይመጣ ዘንድ የታገሉ የኦሮምያ ቄሮዎች ጠብመንጃ አንስተው ይህንኑ ፓርቲ ገጠሙት። ፓርቲው ከህዝብ ጫንቃ ላይ ሆኖ የይድረስ ይድረስ ተጠፍጥፎ የተሰራ ፓርቲ ስለሆነ ችግር መፍታት ቀርቶ ራሱን ለማትረፍም የማይበቃ ሆኖ ወጣ።  በየጊዜው የሚያስቆጥራቸው የፖለቲካ ኪሳራዎች በእጥፍ እየተባዙ ቀጠሉ። ራሱን ለማትረፍ ሲል ኦሊጋርኬ ፈጠረ። ሀገሩ በሙሉ በዚህ በከሰረ ፓርቲ እየተመራ ግጭት በግጭት ላይ ደማሪ ሆነ። ከአማራ ክልል ለጥቆ ጋምቤላና ቤንሽንጉል ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ገጠማቸው። ኦሮምያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ የነበሩ ወጣቶች ነፍጥ አንስተው የክልሉንም ፌደራሉንም መንግስት ገጠሙ።  ብልጽግና ፓርቲ በከፍተኛ የፖለቲካ ኪስራ መሃል እየነዳ ድርጅታዊ ስካሩ እየጨመረ መጣ። በተለይ ትግራይ ላይ የተደረገው ከፍተኛ ጦርነት በደም ካሰከረው በኋላ የመጣውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ወደ ፖለቲካ ድሎች መቀየር ደግሞ አልቻለም። ብልጽግና ፓርቲ ይህንን ስምምነት ወደ ፖለቲካ ስምምነት ሳይቀይር ትግራይን ውርውሮ ኢትዮጵያ እያንሰራራች ነው እያለ መንዳቱን ቀጠለ። የኢሃዴግ አንድ ቁራጭ የሆነው ህወሃት በትግራይ ውስጥ እጅግ የተደናበሩ ርምጃዎችን ይወስዳል። ተው የሚለው የለም።  

 

ብልጽግና ጋምቤላን የግጭት ማዕከል አድርጎ የኢትዮጵያን ሰላም እናጽና ይላል። ከአማራ ጋር ጦርነት ውስጥ ገብቶ ኢትዮጵያ ታሪካዊ የእድገት ጉዞ ጀምራለች ይላል። ኦሮሞን ሰላም አሳጥቶ ያገኛችሁትን ድልና ሰላም ጠብቁ ይላል። እነዚህ የብልጽግና አባባሎች የድርጅታዊ ቀውስ መገለጫዎች ናቸው። ድርጅታዊ ሰውነቱ በከፍተኛ የስነልቡና ቀውስ ውስጥ መግባቱን ያሳያል። ጦርነቱን ተከትሎ እንዲሁም የድርጅቱን ብልጭልጭ ፕሮጀክቶች ተከትሎ አገሪቱ ያላትን ጥቂት አንጡራ ሃብት በማባካኗ ድህነት በምድሪቱ ስያሜ ታጣለት መምህራን፣ ሃኪሞች ራበን ያሉበት ጊዜ ላይ ወደቅን። ይህ የከሰረ ፓርቲ ይህ ሁሉ ሲሆን እየበለጸግን ነው ይለዋል ለሰራተኛው። ከፍ ሲል እንዳነሳነው ይህ ምላሽ የድርጅታዊ ስነ ልቡና ቀውስ ምልክት ነው። ተቋም እንደ ሰው ነው። ህጋዊ ሰውነት አለው። ይህ ሰው እንደ ሰው ሊበላሽ ይችላል። አንዳድ ወገኖቼ ስለ ህወሃት አንዳንድ መሪዎች ስብዕና ሲነግሩኝ እከሌ እኮ ጥሩ ሰው ነው፣ ከቤቱ በልተህ የጠገብክ አይመስለውም፣ መልካም ስው ነው ይሉኝ ነበር። እኔ ራሴ የማውቀው ከህወሃት ሰዎች መካከል አንዱ በጣም ጥሩ ሰው እንደነበር አውቃለሁ ነገር አንድ ነገር አለ። ድርጅቱ እንደ ድርጅት ተክለ ሰውነቱ ጥሩ ካልሆነ በዚያ ውስጥ አንዳንድ ጥሩ ሰዎች ቢኖሩም ዋጋ የለውም። እነዚሃያ መልካም ሰዎች ታግለው ድርጅቱን ሪፎርም ካላደረጉ የድርጅቱ ሰውነት የተበላሸ ይሆናል። ህወሃት  ስስታም አስተሳሰብና ጠባብ ፕሮራም ይዞ ሳለ በዚያ ውስጥ አንድ ልበ ሰፊ ሰው አለ ቢባል ምን ዋጋ አለው?

 

እንግዲህ ብልጽግና በብዙ ኪሳራ ውስጥ ሆኖ አሁንም እድሜ ጨምሩልኝ የኢትዮጵያን ባቡር ቁልቁል ልንዳ ለማለት ሰባተኛ ምርጫ ደግሷል።  ይህ ፓርቲ በእውነት ተጨማሪ አምስት አመት ቢሰጠው ይህንን ባቡር የት ያደርሰዋል?  ይህ ተሰርቶ ያላላቀ ፓርቲ እንደገና ተጨማሪ አምስት አመት ስልጣን ላይ ቢቆይ ሃገራችን ምን ትሆናለች? ፖለቲካዊ ጉዳያችን ወድቆና ተሰብሮ ከቶ ማረፊያውስ የት ነው? ብለን ስንጠይቅ በዚህ ምርጫ ላይ አንዱ ተወዳዳሪ አደገኛ ተክለ ሰውነት ይዞ ዱብዱብ እያለ ነውና እንደ ሃገር ምርጫን ተስፋ እንዳናደርግ ያደርገናል። ይህንን ፓርቲ ይዘን የምንወጣው ዳገትና የምንሻገረው ወንዝ የለምና ጥሩ እጩ ነህ ቀጥል ልንለው የምንችለው ፓርቲ አይደለም።  

 

 

              ተቃዋሚው ጎራስ? በእርግጥ የዚህ ቀውጢ ጊዜ መሪ ሊሆን ይችላል?

 

የሰባተኛውን ምርጫ ሳስብ በጣም የሚያሳዝነኝና የሚያሳስበኝ የብልጽግና አገር የመምራት ብቃት ማጣትና በመቆየቱም የሚያስከትለው አደጋ ብቻ አይደለም።ተቃዋሚውን ሃይል ሳስብም ምርጫን ተስፋ እንዳላደርግ አድርጎኛል። የምርጫው ተአማኒነት እንዳለ ሆኖ አንድ ህዝብ ወደ ምርጫ ሲገባ ቢያንስ አንድ ጠንካራ ፓርቲ ያስፈልገዋል።

 አሁን ባለው ሁኔታ ሲታይ በተቃዋሚው በኩል ያሉ ፓርቲዎችን ስናይ እጅግ ደካማ ፓርቲዎች ሆነው ለሃገሪቱ ሽግግር በጣም ቀጥነው ይታዩኛል። አንዳንዶቹ ቅንነት ቢታይባቸውም፣ መሪዎቹን የማውቅና የማከብራቸው ቢሆኑም፣ ነገር ግን በዚህ ቀውጢ ሰዓት የመንግስትን በትረ ስልጣን ብቻውን ተረክቦ ይህንን ማዕበል ጸጥ ረጭ አድርጎ ሊመራ የሚያስችል ቁመና ገንብቷል የምንለው ፓርቲ የለም። ይህ የሆነበት ምክንያት አንድም ከራሱ ከብልጽግና ክፋት ጋር የተያያዘ ነው። አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት ጀምሮ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንዳያብቡ እያደረገ ነው የመጣው። ቲም ለማ ወደ ስልጣን ሳይመጣ በፊት በዚያ ህዝባዊ እምቢተኝነት ጊዜ ተቃዋሚው እያደገ ሳይሆን እየከሰመ ነበር የሚመጣው። በብዙ ሃገራት ተመክሮ እንደታየው ህዝባዊ እምቢተኝነት እያየለ በሚመጣነት ጊዜ ተቃዋሚው እየተደራጀ... እያበበ... እየፈረጠመ.... እየተነቃቃ..... ይመጣል። በኛ ሃገር የታየው ግን ከዚህ ተቃራኒ ነበር። ቲም ለማ እያደር እየፈካ እየፈካ እየፈካ ሲመጣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አንድነት ፓርቲ፣ መኢአድ ፓርቲ እየከሰሙ ነበር የሚመጡት። ኢህአዴጎች የሽግግር መንግስት ሃሳብ ጉዳይ እንዳይነሳ ስለፈለጉ ቀደም ብለው ተቃዋሚውን አጭደው በልተው ጨረሱ። ምንም አይነት የሃይል መካፈል (power sharing) እንዳይኖር ተደርጎ ነበር የቲም ለማ እንቅስቃሴ  የተቀረጸው። በመጨረሻ አንዳንድ ለውጡን በጥንቃቄ ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎች፤ የፖለቲካ ሃይሎችን ያሳተፈ፣ ምሁራንን እና ሲቪክ ድርጅቶችን ያሳተፈ የሽግግር ጊዜ ይፈጠር፣ ቲም ለማ ለውጡን ብቻውን ለመምራት ይቀጥናል ብለው ሊመክሩ ቢሞክሩም በወቅቱ የሚሰማ ጠፋ።

 

የሚያሳዝነው አብይ ወደ ስልጣን ከመጣም በኋላ ፓርቲዎች እንዳያድጉ፣ ፕሬስ እንዳያድግ፣ ሲቪል ማህበረሰብ እንዳይገነባ ሲያደርግ ነበር የቆየው። እነሆ ዛሬ አንድም ፓርቲ መንግስትን ተረክቦ ሊመራ የሚችል ቁመና ያለው ፓርቲ አላፈራንም። በዚህ አብይ ተሳክቶለታል። ዛሬ የምናያቸው ፓርቲዎች ሁሉ ከህዝብ ጋር በይፋ ተገናኝተው መክረው አያውቁም። ህዝብ ቁመናቸውን ሊለካ፣ ሊጠይቃቸውና ሊገመግማቸው አልቻለም። ምሁራን በነጻነት ቀርበው በሃሳብ ሊያሳድጓቸው ሊያጎለብቷቸው አልቻሉምና ጥሩ እጩ መንግስት ሊያደርጓቸው አልቻሉም። ድርጅታዊ አቅማቸውን ለመገንባት በየወረዳው በየቀበሌው ጽህፈት ቤት ከፍተው ህዝባዊ መሰረት ሊይዙ የተደበቁ ታለንቶችን አውጥተው ፈልፍለው ራሳቸውን ሊያበቁ፣ አዳዲስ መሪዎችን ሊያበቅሉ አልቻሉም። ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ስላለባቸው የተደራጀ መረጃ ሊያከማቹ በመረጃና ጥናት ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ሊነድፉ አልቻሉም። ኢትዮጵያን በምልዓት ሊያውቁ ሊጎበኙ አልቻሉም። የተሻሉ መሪዎች ሲያገኙ መሪዎችን ማሰርና ማሳደድ የአብይ አህመድ ዋና ዘመቻ ስለሆነ ፓርቲዎች በተሻለ የሰው ሃይል ራሳቸውን አላበቁም። የዚህ  ችግር ክፋቱ ጎልቶ የሚታየው ታዲያ ሃገራዊ ምርጫ ስናስብ ነው። በመንግስትና በፓርቲ መካከል ጋብቻ ስናስብና የምርጫ ሰርግ ድግስ ስንደግስ ነው ችግሩ ጎልቶ የሚታየው።  ዛሬ ላይ ሆነን ስለ ሰባተኛው ምርጫ ስናስብ እነዚህ ችግሮች  ግዙፍ ሃገራዊ ችግሮች  ሆነው ይታዩናል። ፓርቲዎች በዚህ ሰዓት በሃቀኝነት ካለብኝ ጫና የተነሳ ጠንክሬ መውጣት አልቻልኩም ስለዚህ አሁን ምርጫ ሳይሆን ሽግግር ጊዜ ያስፈልጋል። የምርጫ መደላድል ሰርተን መሰላል ዘርግተን ወደ ምርጫ እንገባለን የሚል ሃቀኛ ውሳኔ ይጠበቅባቸው ነበር። ከዚህ ይልቅ ህዝቡን የተሻለ አሳብ አለኝ እያሉ አቅም እንዳለው ሰው መቅረባቸውን አልደግፍም። እውነተኛ ምርጫ እንኳን እናድርግ ቢባል ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊመርጠው የሚችለው አንድም ፓርቲ የለውም። ይህ ከፍተኛ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ችግር ብቻውን አገሪቱ ቆማ እንድታስብ የሚያደርግ ጉዳይ ነበር። ጊዜው የግድ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስትን ውለዱ የሚልበት የመታጠፊያ ምዕራፍ ላይ ነን። የሽግግግር ጊዜ ፈጥሮ ለፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ፓርቲዎች ፈርጥመው ሲያበቁ ምርጫ ብንል ያምራል። እንግዲህ በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ ወስጥ ምርጫ እንዳይካሄድ አንድ ቀይ መብራት የሚያሳየው ችግር ይህ የፓርቲዎች ቁመና ጉዳይ አንድ ዋና ጉዳይ ነው።


 
ምርጫን እቃወማለሁ! አካታች የሽግግር መንግስት ይቋቋም

                             

 

 

 

 

2.    ሃገራችንን ከውጪ ጣልቃገብነት ለመጠበቅና ብሄራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር

 

ሌላው በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት እንድታቋቋም ገፊ የሆነው ብርቱ ጉዳይ የቀጣናው ፖለቲካና አለማቀፋዊ ለውጦች ናቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ አንባቢ ሆይ ትንሽ ሰፋ አድርገን ወደ ኋላ ወደ ፊት እያልን እንወያይ። በቅድሚያ በተለይ ለወጣት ፖለቲከኞች ግንዛቤ ሊያግዝ ስለሚችል በተለይ የአሜሪካንን እና የቻይናን እንቅስቃሴዎች እንመልከት በመጨረሻም በቀጥታ ወደ ሃገራችን እየተወረወረ ያለውን የገልፍ ሃገራት ፍላጎት እንመለከታለን። የቻይናንና የአሜሪካንን ጉዳይ የምናነሳው አጠቃላይ አለማቀፋዊ ለውጦችን በመጠኑ መገምገሙ ተገቢ ሆኖ ስላገኘነው ነው።

 

ሁላችን እንደምንታዘበው አለማቀፋዊ የሃይል አሰላለፎች  በከፍተኛ ሁኔታ ለውጦችን እያሳዩ መሆናቸው በግልጽ የሚታይ ጉዳይ ሆኗል። በተለይም የልዕለ ሃያል ሃገር አሜሪካ ተለዋዋጭ የውጭ ፖሊሲ ለውጦችና የቻይና የኢኮኖሚ ጥርመሳን ተከትሎ በዓለም ላይ የነፈሱ የፖለቲካ ዲስኮርች ሞልተዋል። አንዳንዶች አሜሪካ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ውስጤ እመለከታለሁ፣ እኔ የዓለም ፖሊስ አይደለሁም፣ እያለች በመምጣቷ፣ አልፎ ተርፎም ይህቺ ሃገር በገንዘብም በእውቀትም በመደገፍ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ከምትይዝባቸው ትላልቅ አለማቀፍ ተቋማት ውስጥ ለምሳሌ ከአለም ጤና ድርጅት፣ ከተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንዳንድ ተቋማት ውስጥ መውጣቷን እየጠቀሱ አሜሪካ ተዳክማለች ይላሉ። ይህቺ ሃገር ከዓለም አጠቃላይ ሃብት ወደ ግማሽ የተጠጋውን የያዘች ሃገር ስትሆን ከአለም ዓቀፍ መድረኮች እየራቀች ትሂድ እንጂ በአለም ዓቀፍ ንግዷ ግን በዚህ ልክ እየቀዘቀዘች አልመጣችም። ፕሬዝዳንት ትራምፕም ሆኑ ፓርቲያቸው ሪፐብሊካን በንግድ ትስ ስር በጣም የሚያምኑ ናቸው። አንዳንድ ወገኖች የቻይናን የንግድ ስኬት እና ወታደራዊ አቅሟን እያዩ ይህቺ ሃገር በቀጣይ የምትመጣውን አለም መሪ አድርገው እያቀረቡ ይገኛሉ። አጠቃላይ የአለም ስርዓት በቻይና ቀዳሚነት እየተተካ እንደሆነም ይገልጻሉ። ስለዚህ አገሮች አሰላለፋችሁን አስተካክሉ ወደ ቻይና አዘንብሉ ይላሉ። ኢትዮጵያም ውሥጥ ይህ ተረክ ይደመጣል። በርግጥ ታዲያ ይህ ድምዳሜ ብዙ ተለዋዋጮችን የተመለከተና የተቆጣጠረ አይመስልም። በርግጥ ቻይና በምጣኔ ሃብት እድገት ረገድ ያሳየችው ሩጫ የሚደነቅ ነው። በጥቂት አመታት ውስጥ በምድሯ ውስጥ በቀን ከሁለት ዶላር በታች የሚያገኝ የድሃ ድሃ ወደማይኖርበት ደረጃ ላይ አድርሳ የከፋ ድህነትን ዱቄት ያደረገች ጀግና ሃገር ናት። ይሁን እንጂ ቻይና በአጠቃላይ ምርት (GDP) ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ብትሆንም በግለሰብ አመታዊ ገቢ መጠን ደግሞ ወደ ሰማኒያኛ የተጠጋች አገር ነች በዚህ ሰዓት የቻይና ሩጫ ይህንን ለመቀየርና የዜጎቿን ምጣኔ ሃብት ደረጃ ወደ አንደኛው አለም ለመቀላቀል ነው እንጂ ቻይና በምትመጣው አለም ላይ ሁለንተናዊ ተጽዕኖ ያላት የዓለም መሪ ለመሆን የምትጥር አገር አይደለችም። በዓለም ላይ ገበያ ለማግኘትና ሸቀጦቿን ለመሸጥ የምታደርገውን ሩጫ እያዩ የወደፊቷ የአለም መሪ የሚሏት ሰዎች ሩጫዋን በሚገባ የገመገሙ አይመስሉም። ይህቺ ሃገር እንደነ አሜሪካ በዓለም ላይ ከባድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ለስላሳ ሃይል (soft power) አልገነባችም። ያላት ጠጣር ሃይል ማለትም ሚሊተሪዋና ኢኮኖሚዋ ጠንካራ ቢሆንም  ለስላሳ ሃይላትን አልገነባችም። ለዚህም ፍላጎት ያላት አገርም አትመስልም። የአሜሪካ ተጽዕኖ የመጣው በጠጣር ሃይል አቅሟ ብቻ ሳይሆን ባሏት ለስላሳ ሃይሎች ጭምር ነው። ወደ ኋላ የአሜሪካንን ታሪክ ብናይ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (USAID) የተቋቋመበት አንዱ ምክንያት ይህቺን ሃገር ሃያል ለማድረግ ለስላሳ ሃይል አስፈላጊ ስለነበረ ነው።

ወደ ቻይና ስንመለስ እስካሁን ድረስ ይህቺ ሃገር የጀነሬሽን ዚን ጥያቄ ሊያግዝ የሚችል የዴሞክራሲ መጽሃፍ አንድም አልጻፈችም። የገነባችው የሰብዓዊ መብት ድርጅት አንድም የለም። የምታበረታታውና የምትደግፈው ነጻ ሚዲያ የሚባል አንድ የለም። በአለም ዙሪያ ሚዲያ ያብብ ዘንድ አስባ ስለ ሚዲያ ነጻነት ተጨንቃ አንድም ተቋም ገንብታ ለዓለም ፕሬስ ነጻነት አትታገልም። እንዴውም ነጻ ፕሬስን ስታኮሥሥ ትገኛለች አለም ያለውን የሃይማኖት ብዝሃነት ለማስተናገድ የሚችል መጽሃፍና የብዝሃነት (pluralism) ንድፈ ሃሳብ አላፈለቀችም።በሰው ሃገር ጣልቃ አልገባም” ስትል ትደመጣለች እንጂ በዓለም ላይ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት እንዲያድግ አንድም አስተዋጾ አታደርግም። የሰብዓዊ እርዳታ ምላሾቿም በጣም ውሱን ናቸው። በአጠቃላይ ቻይና የኢኮኖሚ እድገት ግንብ ትሰራለች እንጂ የለስላሳ ሃይል ግንባታ ሙከራ አታደርግም። በዚህ አያያዟ ቻይና ይህቺን አለም በተለይም የምትመጣውን አለም ለመምራት አትችልም።  ጀነሬሽን የሚጠይቀውን የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ትምህርቶችን በፊት አውራሪነት ልትመራ ዝግጁ አይደለችም።

በዓለማችን ታሪክ ውስጥ የዓለም ሰርዓት ከባድ ውጥረት ውስጥ ገብቶ የነበረው በሶሻሊዝም ጊዜ ነበር። ሶቪየት ህብረትና ሶሻሊስት ሃገሮች ይህ ዓለም የሚተዳደርበትን የተሻለ አስተዳደር ዘዴ አግኝተናል ሲሉ መጽሃፍ ጽፈው፣ ለኢኮኖሚ ክፍፍል የተሻለ ንድፈ አሳብ አለን ብለው፣ ኢንተርናሲዮናል የሚባል መዝሙር ደርሰው የምዕራባውያንን ንባብ በእጅጉ ሞግተውት ነበር። እንደውነቱ አለምን አንገዳግደውት ነበር። ቀዝቃዛው ጦርነት ስሙ ቀዝቃዛ ይባል እንጂ ኮሚኒዝም የብዙ አለም ወጣቶችን ቀልብ አሙቆና አግሎት ነበር።  ይሁን እንጂ ዝግ እያለ የምስራቁ አስተሳሰብ ተሸንፎ የምዕራቡ አስተሳሰብ አሸንፎ ወጥቷል። ራሽያም ያንን የኮሚኒዝም ትምህርቷን አውልቃ ጥላ የአሜሪካንን የፌደራል ስርዓት ተከታይ አገር ሆናለች ። በርግጥ ከገጠማት የኢኮኖሚ ኪስራ እያንሰራራች ጠጣር አቅሟንም እየገነባች ነው። ይሁን እንጂ ገና ብዙ የሚቀራት ሃገር ናት ። ዛሬ  የአለም እዝ በዚሁ በካፒታሊስቱ አሳብ ተቃኝንቶ የምዕራቡ  አለም ፍልስፍና እስካሁን ይኖራል። በነገራችን ላይ ቻይና እስካሁን ያንን የተሸነፈ የኮሚኒዝም ስርዓት በህገ መንግስቷ ላይ እንደቀረጸች ነው። ህግ የሚተረጉመው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ነው። ምንም እንኳን በኢኮኖሚው መስክ የተለያዩ አስተሳሰቦችን እየቀየጠች ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ብታመጣም የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳይ የዴሞክራሲ አስተሳሰቦቿ ከቶውንም እድገት አያሳዩም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ቻይና ወደፊት የአለም ፊት አውራሬ ልትሆን አትችልም። ቻይና ብቻ ሳትሆን የእስያ ሃገራት በዚህ ማዕቀፍ የሚታዩ ናቸው። ወደፊት ምን አልባትም ቻይና ውስጥ ህዝቡ በኢኮኖሚ በሚገባ ካገገመ በኋላ የቻይና ጀነሪሽን አብዩት ሊያስነሳም ይችላል። ገና አብዩት የሚጠብቃት ሃገር ወደፊት የዓለምን ስርዓት ለመምራት ቀንዲል ናት የሚለው አስተሳሰብ የቻይናን ቁመና በሁለንተናዊ መልኩ ያላገናዘበ ነው የምንለው ለዚህ ነው። የሰው ልጅ ውስብስብ ፍላጎት ያለው በመሆኑ የኢኮኖሚ እድገት ብቻውን ሁለንተናዊ ፍላጎቶቹን አያሟላምና ቻይና ውስጥ አብዩት የሚቀር አይመስልም። ከፍ ሲል እንዳነሳነው ቻይና ድህነትን በመቀነስ ረገድ ምሳሌ የምትሆን አገር ብትሆንም አለማቀፍ ተጽዕኖዋ ረጅም ጊዜ የሚቆይ የአለምን ህዝብ በአዲስ አስተሳሰብ የገዛችና የማረከች ሃገር  ግን አይደለችም። በአፍሪካ ሃገራትም ይሁን ዴሞክራሲ በዳዴ በሚሄድባቸው ሃገራት ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከቻይና ጋር ሲሰሩ ወጣቱ ወደ ቻይና ደብዳቤ ሲጽፍ አይታይም። ከፍ ሲል እንዳልኩት ጀነሪሽን ዚን ለማገዝ የምታደርገው ጥረትም ስለሌለ ቻይና ያላት ተጽዕኖ ዘመን ተሻጋሪ አይደለም። ይህቺ ሃገር ስልጣን ላይ ያሉትን በመደገፍ ጊዜያዊ ንግድ ከማካሄድ ያለፈ ብዙ ህልም ያላት ሃገር አይደለችም። በዚህ መሰረት አምባገነን መንግስታት የቻይናን ሞዴል እንከተላለን እያሉ ሲናገሩ ይደመጣል። በርግጥ ቻይና በድህነት ቅነሳ እርምጃዋ ምሳሌ የሆነች አገር ናት ነገር ግን በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት በሚዲያ ነጻነት ዙሪያ ግን ምሳሌ የምትሆን አገር አይደለችም።

በዚህ ወቅት በአለም ላይ ተጽዕኖ ይዞ መጥቷል የሚሉት ብሪክስም ቢሆን ለጀነሪሽን ተስፋ አላሳየም። ከመነሻው እነዚህ በብሪክስ ውስጥ ያሉ ሃገራት አንድ ላይ ተሰባስበው የጻፉት መጽሃፍ ወይም የነደፉት ንድፈ ሃሳብ የለም። ዶላርን ድባቅ መትተን የብሪክስን መገበያያ አሸናፊ እናደርጋለን ይላሉ። ይህ በጣም የተሳሳተ ሮድ ማፕ ነው ይባላል። ኢኮኖሚ በመሰረቱ ህልው ያለው በፖለቲካል ኢኮኖሚ ውስጥ ነው። ፖለቲካል ኢኮኖሚ እና ርዕዮት ይጠይቃል፣ ኢኮኖሚ። እነዚህ የተለያየ ርዕዮት ያላቸው የብሪክስ ሃገራት የአለም አቀፍ ግንኙነትን የሚቀይሩበትን ንድፈ ሃሳብ ማቅረብ ቢችሉ ነበር ተገዳዳሪ የሚሆኑት ይህ ግን አይታይም። ከዚህ በተጨማሪ ብሪክስ የኢኮኖሚ እድገትን ከዴሞክራሲና ከሰብዓዊ መብቶች ነጥሎ ማየቱ በተለይ ከምትመጣው ዓለም ወይም ከጀነሬሽን ጋር ያጋጨዋል። ስለዚህም ብሪክስ ልዕለ ሃያል ይሆናል የሚለው በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ትርክት በዚህ ረገድ ውሃ አያነሳም። በመሰረቱ ወደፊት የምትመጣዋ አለም ጥቂት ሃያላን ሃገራት የሚተውኑባት ሳትሆን የተሻሉ አለማቀፋዊ ተቋማት ተገንብተው አለም የተሻለች ትሆን ይመስላል። የ AI ትውልድ በሳይንሱ እያደገ ደግሞ ጥሩ ጥሩ አለማቀፋዊ ተቋማትን ግንብቶ የአለምን ስርዓት ማሻሻሉ አይቀርም።

ውድ አንባቢ በርግጥ የዚህ ጽሁፍ ጭብጥ ሽግግር መንግስት በኢትዮጵያ ለምን ያስፈልጋል? የሚለውን ሃሳብ ለመሞገት ነበር። ወደ አለም አቀፉ ጉዳይ ይህን ያህል የገባሁት በተለይ ወጣቱ ትንሽ ይጠቅመው እንደሆነ በሚል ነው። ይህንን ጉዳይ በዚሁ እንቋጭ እና ከፍ ሲል እንደ ገለጽኩት ቻይና ለኢኮኖሚ እድገቷ የምትጋልብበት ዓለም ሲሮጥ በአንጻሩ በሰብዓዊ መብት ጉዳና በዴሞክራሲ ጉዳይ ሲሰሩ የነበሩት የምዕራብ ሃገራት ወደ ውስጥ ጉዳይ ትኩረት አድርገው  ሲሮጡ መካከለኛ ሃይላት (midle power) ሃገራት ደግሞ ከመቼውም በላይ እንደ ተራበ ነብር ሆነው ሲሯሯጡ ይታያል። በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ መካከለኛ ሃያላን  የሚባሉት ሃገራት ማለትም ሳውዲ አረቢያ፣ ኤምሬትስ፣ ቱርክ፣ እስራኤልና ኢራንን ያካትታል። ኢራን በሶሪያ ውስጥ የአሳድን መንግስት አጥብቃ ትደግፍ የነበረች አገር ነበረች ። አሳድ ዙሪያውን ተከቦ ባለበት ሰዓት ሁሉ በመሳሪያ፣ በገንዘብ፣ በስልጠና፣ በቴክኖሎጂ ትደግፍ ነበር ። ኢራን ሌላኛው ለረጅም ጊዜ የምትደግፈው ሃይል ደግሞ ህዝቦላ ነው። እስራኤልን ለመገዳደርና በአካባቢው ተጽዕኖዋን ለማስፋት ነው ይህንን የምታደርገው። ነገር ግን አሁን በአፍሪካ ቀንድ ላይ ባለው የኤምሬትና የሳውዲ አረቢያ ትንቅንቅ ውስጥ ሶስተኛ ተዋናይ ሆና እምብዛም አትታይም። ለዚህ ምክንያቱ መንግስቷ በህዝባዊ እምቢተኝነት እየተናጠ ስለሆነ ነው። የአረብ ስፕሪንግ የዘለላት ኢራን ዛሬ እየናጣት ይገኛል። በዚህ ምክንያት የጎላ ተጽዕኖዋን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አናይም።

እስራኤል ለሶማሌላንድ እውቅና መስጠቷ የሚያሳየው አንድ ነገር መካከለኛው ምስራቅ በሃይል ወደ አፍሪቃ ቀንድ እየተሳበ መሆኑን ነው። ይህቺ ሃገር ጎረቤቶቿ የአፍርካ ቀንድን ለመቆጣጠር የሚደርጉት  ሩጫ ስላሰጋት የኤደን ባህረ ሰላጤ በር የሆነችውን ስትራተጂክ ቦታ ለመቆጣጠር እየሰራች ነው።

ቱርክ በበኩሏ ቀደም ሲል በሶርያ የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እጇ ያለ ሃገር ነበረች ። በተለይ በሰሜናዊ ሶርያ ግዛት ከፍተኛ ተጽዕኖ ነበራት። የአሳድን ተቀናቃኞች ስትደግፍ የቆየች አገር  ናት ። ቱርክ አፍሪካ ቀንድ ላይ ካሉ ሃገራት መካከል ብዙ ኢንቨስት ያደረገችው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ወደ 260 የሚሆኑ ካምፓኒዎች አሏት ። በግብርና፣ በማሽነሪ እና በጨርቃጨርቅ ላይ በሰፊው ትነግዳለች ። ከቻይና ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ብዙ ኢንቨስት ያደረገች አገር ቱርክ ናት። ስለሆነም ኢትዮጵያ ላይ ከፍ ያለ ዝንባሌ እንዳላት ልብ ይሏል። ይህቺ አገር ዛሬ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ከፍተኛ ዝንባሌ ካሳዩ ሃገራት አንዷ ናት። ሱዳን ውስጥ የሱዳንን ጦር የምትደግፍ ሲሆን ፈጥኖ ደራሹን ከሚያወግዙ አገራት አንዷ ናት። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ ፈጥኖ ደራሹን የሚደግፍ በመሆኑ በዚህ ረገድ ግጭቶች አሉ።

 እነዚህ የመካከለኛው ምስራቅ መካከለኛ ሃያላን ሃገራት የያዙት ሩጫ ለሃገራቸው ኢኮኖሚ ተጨማሪ እሴት ለማምጣት ቢሆንም የሚሄዱበት መንገድ ግን እጅግ አደገኛ ነው። በኢኮኖሚ ደካማ የሆነውን የአፍሪካን ቀንድና መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ  ያሉ አንዳንድ ደካማ ሃገራት የውስጥ ፖለቲካ ውስጥ በመግባት በየ ሃገሩ አንድ ሁነኛ መሪ ለማስቀመጥ በሚያደርጉት እሽቅድምድምና ፍትጊያ የቀጣናውን ሃገራት አገረ መንግስት እያፈረሱ ነው።

የአረብ ስፕሪንግ ሲነሳ መነሻ ላይ ፕሬዝዳንት ኦባማ ከፍተኛ ድጋፍ ያሳዩ ቢሆንም በመካከል በተለይም ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስና ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ውስጡን ከአረብ ስፕሪንግ ቀጥሎ የሚመጣውን መንግስት በእጅ አዙር የነሱ መጠቀሚያ ለማድረግ ባደረጉት ሩጫ የአረብን ስፕሪንግ ወደ አረብ ቃጠሎ ቀይረውታል። ኤምሬት በየመን የደቡብን የሽግግር ምክር ቤት (TNC)  እየደገፈች ቆየች። ይህ ቡድን ደቡብ የመንን እገነጥላለሁ የሚል ህልም ያለው ነው። በሌላ በኩል ሳውዲ አረቢያ አለማቀፍ ተቀባይነት አለው የሚባለውን የየመን መንግስት ትደግፋለች በርግጥ የሳውዲ ድጋፍ ለየመን መረጋጋት የተሻለ ቢሆንም ኤምሬትስ በሌላ በኩል ገንዘቡ ስላላት ተገንጣዩን በማገዟ የየመን ስፕሪንግ ወደ ንዳድ ተቀይሮ ቆየ። ለአረብ ስፕሪንግ ኪሳራ ተጠያቂዎቹ እነዚህ የገልፍ ሃገራት ብቻ ናቸው ማለት አይቻልም። አሜሪካና ምዕራብ ሃገራትም የሚወስዱት ድርሻ ይኖራል። ነገር ግን እነዚያ ሁለት ሃገራት በተለይ ግዙፍ ድርሻ እንዳላቸው አይካድም። ከፍ ሲል እንደ ገለጽነው ሶርያ ውስጥ የአረብን ስፕሪንግ ተከትሎ የተለያዩ እጆች ገብተው ነበር። የኢራን፣ የቱርክ፣ የራሽያ፣ የአሜሪካ እጆች ገብተው የተለያዩ ቡድኖችን እያፋፉ ቆይተው ኋላ ላይ ሶርያን እሳት እንዲበላት አድርገዋል። ሊቢያ ውስጥ ኤምሬት አንድ ጊዜ የምስራቁን የሊቢያ ብሄራዊ ጦር ትደግፋለች ቆየት ብላ ደግሞ የፖሊሲ ለምጥ አምጥቻለሁ ስትል እንሰማለን። ሳውዲ በበኩሏ ይህንኑ ሃይል ስትደግፍ የቆየች ሲሆን ውስጥ ለውስጥ ግን ከፍተኛ የሃይል ፍክክርና ሽኩቻ ያሳያሉ።

ወደ ጎረቤት ሃገር ሱዳን ስንመጣ የሱዳን ህዝብ የዳቦ ዋጋ ጨመረ ብሎ አልበሽርን ከጣለ በኋላ ለውጡ በመጠለፉና ወታደሩ በመሰባበሩ ለአደጋ ተጋለጠ። በዚህ መሃል ሳውዲ የሱዳንን ብሄራዊ ጦር ስትደግፍ ኤምሬት ፈጥኖ ደራሹን ደግፋ ሱዳን ፈረሰች ዛሬ ሱዳን ውስጥ ከነዚህ ሁለት በግልጽ ከሚታዩ ሃገራት ውጭ እነ ቻይና፣ ራሽያና ሌሎች ሃገሮችም ሱዳንን እያተራመሱ ይገኛሉ።

ጎበዝ አሁን ወደ ቤታችን እንመለስ። ተመልከቱ፣  በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ዋናው ጉዳያችን በኢትዮጵያ ውስጥ አስሸኳይ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ያስፈልጋል ለሚለው ሙግታችን ይህንን አካባቢያዊ ጉዳይ ለምን ዳሰስን? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ይህንን አለማቀፋዊ ጉልህ ጉዳይና የአረብን ስፕሪንግ ያነሳንበት ዋና ጉዳይ ሁለት ነው። አንደኛውና ዋናው ጉዳይ  እነዚህ ተገንጣይና ፋክሽን እየፈለጉ፣ የተለያዩ ሃይሎችን እየደገፉና እየደለሉ፣ ሀገረ መንግስት የሚያፈርሱ የውጭ ሃይሎችን ለመቋቋም ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ማቋቋምና ቶሎ ብለን የብረት አጥር መስራት ምን ያህል ወቅታዊና አዳኝ አሳብ መሆኑን ለማስረገጥ ነው። የአረብን ስፕሪንግ ያፈረሱ የውጭ ሃይላት ዋናው መሳሪያቸው አኩራፊ ሃይሎችን ማፈርጠም፣ ተገንጣዮችን ማፋፋት፣ ሁለትና ከሁለት በላይ የሆኑ የሃይል ማዕከላትን በመፈልፈል ከፍተኛ ቅራኔ በመፍጠር አገርን ማተራመስ፣ የስልጣን ፍቅር ያለውን ሰው በመደገፍ መንግስትን መጥለፍ (state capture) የነዚህ የውጪ ሃይላት ዋና ዘዴ ነው። በዚህ ዘዴ እነሆ የመን ፈረሰች፣ ሊቢያ ፈረሰች፣ ሱዳን ፈረሰች፣ ሶርያ ፈረሰች።  

ዩናይትድ አረብ ኤምሬት በኢትዮጵያ ውስጥ ህልውናዋ የጎላ እንደሆነ ብዙ መረጃዎች ወጥተዋል። ይህቺ ሃገር ከዚህ በፊት በሶማሊያና በሱዳን ውስጥ በየመንና ሊቢያ ውስጥ ህልውናዋ የጎላ የነበረ ሲሆን አሁን ከነዚህ ሃገራ እየተሸነፈች እየወጣች ነው ። እንደሚታወቀው ሱዳን ውስጥም እሷ የምትደግፈው ፈጥኖ ደራሹ እያፈገፈገ ይገኛል። ይህቺው ሃገር ይህንን የሱዳንን ፈጥኖ ደራሽ በምዕራብ ሊቢያና በሶማሊያ በኩል ታስታጥቅ የነበረ ሲሆን የሶማሊያና የሊቢያው መስመሮቿ በሳውዲ የበላይነት ሲዘጉባት እነሆ ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ መጥታለች። በሳተላይት የተደገፉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአብይ አህመድ መንግስት የኤምሬትስ  ደጋፊ ሆኖ ዛሬ ቤንሻንጉል ውስጥ የሱዳንን ፈጥኖ ደራሽ እያሠለጠነ ነው። ይህ ጉዳይ ብሄራዊ ጥቅማችንን በሃይል ይጎዳል። አንዱ የኤምሬት ህልውና በኢትዮጵያ መብዛቱን የሚያሳየው ይሄ ሁኔታ ነው። በቅርቡ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ላይ የወጣ ትንተና እንደሚያሳየው ኤምሬትስ አብይ ወደ ስልጣን እንደ መጣ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ለግሳዋለች ይህ ገንዘብ የዋለው የዚህን ሰው ስልጣን ለማጠናከርና የዚህን ሰው ጥበቃዎች ለማጠናከር ነበር። ይህቺ ሀገር ዝግ እያለች ደህንነቱን በመቆጣጠር ስር የሰደደች ይመስላል። ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እጅግ ያሳስበናል።

በ2024 ዓመተ ምህረት ሮይተርስ አንድ አስደንጋጭ የምርምር ዘገባ ይዞ ወጥቶ ነበር። ይህ ዘገባ እንደሚያሳየው አብይ አህመድ ወደ ስልጣን እንደ መጣ በወራት ውስጥ ኮሬ ነጌኛ የተባለ መንግስትን የሚጠልፍ (state capture) አደረጃጀት ፈጥሮ እንደሚንቀሳቀስ ተዘግቧል። ይህ  አደረጃጀት ሲጠነሰስ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እጅ ይኖርበታል። ገና ከመነሻው አብይ አህመድን ወደ ስልጣን አምጥቶ ይህንን ሰው መጠቀሚያ ለማድረግ ኤምሬትስ ተዘጋጅታ እንደነበር መገመት እንችላለን ። ዛሬ ይህቺ አገር የእምዬ ምኒልክን ቤተመንግስት እየቀየረች እጅግ ትልቅ ቤተመንግስት እየገነባች ነው። በነገራችን ላይ አብይ አህመድ መጀመሪያ ላይ ስልጣን ሲረከብ ኤምሬት ታላቅ ደስታ ላይ ነበረች ። የአብይንና የቢን ዛይድን ፎቶ በህንጻ ላይ አሸብርቀው ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር።

በአጠቃላይ በዚህ ወቅት የገልፍ ሀገራት የጥቅም ትርምስ በአፍሪካ ቀንድ ላይ በሃይል ጎልቶ የሚታይ ሲሆን ዋና ዋና ተጠቂ ሃገራት ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራም ጭምር ሲሆኑ ኬንያ ግን እስካሁን ተጽዕኖው ጎልቶ የማይታይባት ሃገር ሆናለች። በጥንቃቄ ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ጥረት እያደረገች ይመስላል።

እስቲ ተመልከቱ፣  የሱዳን ህዝብ የተሻለ ስርዓት ለማምጣት ነበር የታገለው። ነገር ግን ዛሬ የሱዳን ልጆች ለሁለት ተከፍለው የሱዳን ህዝብ ሽግግር እንዳያይ አድርገውታል። ፈጥኖ ደራሹ በኤምሬት ዋናው ጦር በሳውዲና ቱርክ እየተደገፉ እርስ በርስ እየተጫረሱ ነው። ታዲያ ይህ ችግር ዳዴ እያለ ወደ ሃገራችን እንዳይመጣና  የሱዳን እጣ ፈንታ እንዳይገጥመን የተለያዩ ሃይሎች የሃይል ክፍፍል የሚያደርጉበትን የሽግግር ጊዜ ፈጥረን አጥራችንን እናጥብቅ ነው የምንለው። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያን ሁሉን አቀፍ የሽግግር ጊዜ ውስጥ ከገቡ በዚህ ባሰፈሰፈ የውጭ ጣልቃገብነት ዘመን ንፋስ አናስገባም አሉ ማለት ነው። የተለያዩ ፍላጎቶችን ያቀፈ የሽግግር መንግስት ውስጥ ስንገባ እና ሃይል ስንካፈል ግጭቶችን ስንቀንስ በዚህ ከባድ ማዕበል መሃል መርከቧን በሸጋ ሁኔታ መቅዘፍ እንችላለን።  ጎበዝ ሌላው ሁለተኛው ጉዳይ የስብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ መብት ድምጾች በዓለም አደባባይ ላይ እየሳሱ ይገኛሉ። የተባበረችው አሜሪካ ከዚህ በፊት እንደ ለስላሳ ሃይል ያገለገሏትን አለማቀፍ ተቋማት ጥላ እየወጣች ነው።  በዚህ ወቅት እኛ ኢትዮጵያውያን የተሳካ ሽግግር በማድረግ ዴሞክራሲን በሰማያችን ስር ልንጠብቀው እንችላለን። ብዙ ሲቪክ ደርጅቶችን በመፈልፈል ለህዝባችን ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ረሀብ ጥጋብ እንሆናለን። የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት ሰላምና መረጋጋትን ልናመጣ እንችላለን። እንግዲህ አንዱ በዚህ ሰዓት የሽግግር መንግስት የማቋቋም መታጠፊያ ምዕራፍ ላይ ነን የሚያሰኘን አንድም በዚህ አለማቀፍዊ ሁነት መሃል በጥሩ መቅዘፍ እንድንችል እና ብሄራዊ ጥቅማችንን አገረ መንግስታችንን ለመጠበቅ ነው። አሁን ያለንበት ሁኔታ ምርጫ ሳይሆን አካታች ሽግግር ይላል።


  
ምርጫን እቃወማለሁ! አካታች የሽግግር መንግስት ይቋቋም



 አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጣ ጊዜ አቡዳቢ ላይ የነበረ ፌሽታ

 





3.    በአፍሪካ ቀንድ ላይ ደቃቃ አገሮችን ለማዋለድ የሚደረገውን ጥረት ለመመከት

አፍሪካ ቀንድ ላይ ወደ አስር የሚጠጉ አገር የመሆን ንቅናቄዎች አሉ። ሶማሊያ ውስጥ ካሉ ስድስት የፌደራሉ አባል ግዛቶች መካከል ሶስቱ አገር መሆን የሚያምራቸው ናቸው። የሶማሌ ላንድ የቆየ ጥያቄ ሲሆን ፑንት ላንድ እና ጁባ ላንድ ሃገር የመሆን ስሜታቸው ከፍተኛ ነው። በቅርቡ የጁባ ላንድ ፓርላማ ከሶማሊያ ፌደሬሽን ወጥቻለሁ ብሎ ወስኗል። አሁን ባለው ሁኔታ ማዕከላዊ ሶማሊያ፣ ጁባላንድ፣ ሶማሌላንድ፣ ፑንትላንድ የተለያየ አገር እየሆኑ ነው። ሶማሊያ አራት ሃገር የመሆን ችግር ላይ ተጥዳ ያለች ሃገር ናት። ማዕከላዊ ሶማሊያም የአልሸባብ ግዛት ነው ማለት ይቻላል።  ወደ ሱዳን ስንመጣ ሁላችን የምናስታውሰው የዳርፉሩ እልቂት ጋብ ብሎ ሰሜን ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ከተፋቱ በኋላ አሁን ሱዳን ውስጥ ያለው ከባድ ችግር ሰሜን ሱዳንን ሶስት ቦታ ሊሰነጥቃት ይችላል ተብሎ ይፈራል። በአንጻሩ ደቡብ ሱዳን ውስጥ የናት (Naat movement) ንቅናቄ አቅም ያገኘ ይመስላል። የላይኛውን አባይ ተፋሰስ ህዝብ ኑየርን ይዘን አገር እንመሰርታለን የሚሉ ሃይሎች ደቡብ ሱዳን ውስጥ አሉ። ይህ ቡድን ጋምቤላም የኑየሮች አገር ናት ነው የሚለው። የጋምቤላ የጸጥታ ችግር በሃይል የተያያዘው ከዚህ ከናት ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ነው። ወደ ሃገራች ኢትዮጵያ ስንመጣ በህገ መንግስቷ መገንጠልን የፈቀደች ሃገር ስትሆን ጥቂት የማይባሉ አገር የማዋለድ እቅድ ያላቸው ሃይሎችም አሉ። ራሱ ህወሃት ባኮረፈ ቁጥር የራስን እድል በራስ መወሰን የሚለውን ማስፈራሪያ ማምጣቱ የሚታይ ነው። ታዲያ ይህ ሁሉ የመገንጠልና አገር የመሆን እንቅስቃሴ በአፍሪካ ቀንድ ላይ እንዲኖር የሚደግፉ ሃይሎች እንዳሉ አንርሳ። በዚህ ቀጣና ብዙ ትናንሽ አገራት ከተፈጠሩ እነዚያን ደካማ ሃገራት በሞግዚት ስም ይዘን የተፈጥሮ ሃብት እየበዘበዝን እንኖራለን ከሚል ስሌት ነው። የአፍሪካ ቀን በዚህ ልክ አገር የመፈልፈል ችግር ውስጥ በገባበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ይህንን አደጋ  የምንከላከከለው የሽግግር መንግስት መስረተን የተረጋጋ ሃገር መንግስት በመፍጠር ነው። በዚህ ሰዓት ምርጫ መግባባትን አያመጣም።


  
 ምርጫን እቃወማለሁ! አካታች የሽግግር መንግስት ይቋቋም

 

 

  4.  የተንከባለሉ የሃገረ መንግስት ጥያቄዎች አገረ መንግስቱን እንዳይረጋ ስላደረጉ

 

                የታኮማ ድልድይ ታሪክና የኢትዮጵያ ምክክር ነገር

A 1.800-meter bridge that collapsed 4 months after its inauguration under  winds of just 64 km/h - CPG Click Petróleo e Gás

ወደ ዋናው ቁምነገራችን ከመግባታችን በፊት አንድ ታሪክ ላጫውታችሁ። ምን አልባት ህብረታችን የተሰኘውን ፖድካስት አልፎ አልፎ የምትመለከቱ ወገኖቼ አንድ ጊዜ የዚህን ድልድይ ታሪክ አንስቼ መነበሬን ታስታውሳላችሁ። አስተማሪ ስለሆነ በዚህ ጽሁፌ ላይም ደግሜ ላነሳው ነው። ታሪኩ እንደዚህ ነው። አሜሪካን ሃገር ውስጥ ዋሽንግተን ግዛት ውስጥ 1940 ዓመተ ምህረት አንድ ትልቅ ድልድይ ተገነባ። በወቅቱ ይህ ድልድይ ብዙዎችን ያስደመመና የመሃንዲሶች የጥበብ ልህቀት የታየበት ድልድይ ነበር። በጥንካሬውና በውበቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ ባልተለመደ ሁኔታ ይህ ድልድይ በተሰራ በአራት ወሩ ተደርምሶ ቁጭ አለ። አሜሪካውያን ባለሙያዎች ከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ ገቡ። ከወጣው አያሌ ገንዘብ በላይ ድልድዩ የፈረሰበት ምክንያት የብዙ መሃንዲሶችን ትኩረት ሳበና ጥናት ተጀመረ። ከብዙ ጊዜ ጥናት በኋላ ብዙዎችን ያስማማው ውጤት በዚህ ሃገር ውስጥ የምህንድስናን ጥበብ በሃይል ቀይሯል ይባላል። ነገሩ ሲጠና የዚህ ድልድይ መፍረስ ምክንያት ሆኖ የተገኘውና ብዙዎች ያመኑበት ጉዳይ የፊዚክስ ህግ ከሆነው ሬዘነንስ ህግጋት ጋር የተገናኘ ነበር። በፊዚክስ ትምህርት ውስጥ ሬዘነንስ የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ የሚያሳየው ይህ ዓለም ካሉት የተፈጥሮ ቅንብሮች መካከል አንዱ ተመሳሳይ የተፈጥሮ መርገብ (frequency) ያላቸው ነገሮች በተመሳሳይ አብረው የሚረግቡበት ክስተት ነው። ለምሳሌ ተመሳሳይ መርገብ (frequency) ያላቸውን ብርጭቆዎች ጎን ለጎን አስቀምጠን አንዱን ብርጭቆ ከወዲህ በማንኪያ ኮርኮም ብናደርገው ከጎኑ ያለው ብርጭቆ በዚህ በተኮረኮመው ብርጭቆ ልክ አብሮ ይነዝራል። ያልተኮረኮመው ብርጭቆ ከዚህ ከተኮረኮመው ብርጭቆ እኩል ድምጹን አሰምቶ የሚረግብበት ህግ ነው ሬዘነንስ የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ ይላሉ የፊዚክስ ሰዎች የኮረኮምነው ብርጭቆ የተነካውን ያህል ይሄኛው ብርጭቆ ሳይነካ አብሮ ይረግባል አብሮ ይደንሳል። የተፈጥሮ ነገር ይገርማል።

ታዲያ ይህ የታኮማ ድልድይ ለካ የገጠመውም ችግር ይህ የተፈጥሮ ህግ መገጣጠሙ ነበር። ድልድዩ ሲሰራ በአጋጣሚ የድልድዩ የተፈጥሮ መርገብ (frequency) ከአካባቢው የተፈጥሮ መርገብ (frequency) ጋር የተገጣጠም ነበር። በዚህ ምክንያት ድልድዩ ከአካባቢው ነፋስ ጋር ሲደንስ ውሎ አድሮ እንደከረመና በዚህ መርገብ የተነሳ እንደተደረመሰ ይነገራል። ከዚያ ወዲይ መሃንዲሶች የሚሰሩት ድልድይና ፎቅ ተፈጥሯዊ መርገብ (frequency) ከአካባቢው ጋር እንዳይመሳሰል አድርገው ይሰራሉ ይላሉ ባለሙያዎች

ይህንን የፊዚክስ ጽንሰ ሃሳብ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎችም ይጠቀሙበታል። ትምህርቱ ይመስጣቸዋል። በዚህም መሰረት የማንነት ወይም የብሄር ፖለቲካን የሚያጠኑ ሰዎች ይህንን ህግ ይጠቀሙበታል።  ፖለቲካ በተመሳሳይነት ማንነቶች ላይ መርገቡን ከጣለና መሳሳቡን በማንነት ላይ ካደረገ የጋራ የመንግስት መዋቅር መገንባት አይችልም። የሚገነባው የጋራ የመንግስት መዋቅር በዚህ የተመሳሳዮች ፖለቲካ መሳሳብ ይፈርሳል። ፖለቲካችን በማንነት ላይ ሲሆንና አንዱ ማንነት ሲኮረኮም ሌላው የዚያ ማንነት አባል የሆነ ሁሉ ሲረግብ ሌላው ስሜት አይሰጠውም። ትግሬው ሲኮረኮም ትግራዋይ ብቻ በያለበት አብሮ ይረግባል፣ አማራና ኦሮሞ አይረግብም። አማራው ሲኮረኮም አማራ ሁሉ ይረግባል። ኦሮሞና ትግሬ አይረግብም። ኦሮሞው ሲነካ ኦሮሞ ሁሉ በያለበት ይረግባል። ትግሬና አማራ ይህ ኩርኩም አያረግባቸውም። ከፍ ሲል እንደተገለው ተመሳሳይ መርገብ የሌላቸውን ሁለት ብርጭቆዎች አስቀምጠን አንዱን ኮርኩመን ሌላውን ብናዳምጥ ምንም እንቅስቃሴ ወይም ስሞታ አንሰማም። ተመሳሳይ ቋንቋ የማይናገሩ ዜጎች ባሉበት አገር ፖለቲካውን በተመሳሳይ መርገብ ላይ ብናዋቅር አንዱ ሲነካ ወይም ሲኮረኮም ሌላው አይሰማውም። ደንዞ ቁጭ ነው የሚለው። አንዱ ሲጠቃ የሚጮኸው የዚያ ብሄር አባል ብቻ ከሆነና ተመሳሳይ የፖለቲካ መርገባችን በዚህ ላይ ከተቃኘ የጋራው ቤት ቅርጸ መንግስታችን ሁሉ እንደ ታኮማ ድልድይ አልረጋ ብሎ ይቆይና ቆይቶ ይፈረሳል። ፌደራል ላይ ያለው አምባገነን ዘውግ ኦሊጋርኬ ፈጥሮ ከተመሳሳይ ማንነቶች ጋር ሲደንስ ከርሞ ይፈርሳል።

ይህንን አስተምህሮ ያመጣሁት አንድም በተለይ የምክክር ኮሚሽኑን ይገልጸው እንደሆነ ትንሽ ይደነግጥ እንደሆነ በሚል ነበር። የምክክር ኮሚሽኑ ተመሳሳይ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች እየሰበሰበ ምክክር ላደርግ ነው ይላል። የተማረኩ ሰዎችን፣ አስመሳይ ተቃዋሚዎችን ከብልጽግና ጋር አገናኝቶ በአንድ ጠረንጴዛ ላይ አስቀምጬ በሃሳብ እንዲዋጣላቸው ላደርግ ነው ይላል። በየወረዳው ብልጽግና የሰጠውን ሰው ሰብስቦ ብሄራዊ ምክክር ላደርግ ነው አሳታፊ ነኝ ይላል። ይህ በተመሳሳይ ሃይሎች መካከል የሚደርግ ብሄራዊ የምክክር ዳንስ እንደ ታኮማ ድልድይ ፈራሽ ነው። ምክክር በመሰረቱ በጣም የተራራቁ ሃይሎችን አገናኝቶ ወደ መግባባት ማምጣት ነው። የሚመሳሰሉ ሰዎችን ሰብስቦ ማስጨብጨብ ምክክር አይደለም።

በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የማይፈታቸውና ሲንከባለሉ የመጡ የሃገረ መንግስት ጥያቄዎች አሉ። እነዚህን ጥያቄዎች እየዘለልን ምርጫ ብናደርግ የረጋ ሀገረ መንግስት መቼም መመስረት አንችልም። አንድ ሃገር ጥሩ መድብለ ፓርቲ ጨዋታ የሚጫወተው ወሳኝ የሆኑ ምርጫ የማይፈታቸውን ችግሮች በምክክር ሲፈታ ነው። በሃገራችን ውስጥ ሲንከባለሉ መጡ የምንላቸው ዋና ዋና የምክክር አጀንዳዎች የሚከተሉት ናቸው። እነዚህን ሳንፈታ ምርጫ ማድረግ እንደ ሃገር አደናቅፎ ይጥለናል።

 

1.    በህብረታችን ወይም በአብሮነታችን ፍፁምነት ላይ

 

ይህ ጉዳይ አንድ ወሳኝ የምክክር አጀንዳ ነው። አሁን ያለው ህገ መንግስት ሃገሪቱን ዘለዓለማዊ አድርጎ አያይም። የማትከፋፈል ኢትዮጵያን ለትውልድ አስልፎ አይሰጥም። በመሆኑም ይህ ጉዳይ ለምርጫ የሚቀርብ ሳይሆን ምክክር የሚፈታው ጉልህ ጉዳይ ነው። በሃገሪቱ ውስጥ በምርጫ ቦርድ ከተመዘገቡት 69 ፓርቲዎች ውስጥ 45 ክልላዊና ብሄር ተኮር ሲሆኑ 24 ደግሞ ሃገር አቀፍ ናቸው። በርግጥ ክልላዊ ሁሉ በዚህ በኢትዮጵያ ዘለዓለማዊ አንድነት ዘሪያ ጥያቄ አላቸው ባይባልም ነገር ግን ይህ አንቀጽ በህግ የሰፈረና ቀላል የማይባል ደጋፊ ስላለው ኢትዮጵያውያን ቁጭ ብለን ልንወያይበትና ይህንን አንቀጽ ለሚደግፉ ዋስትና በማስፋት የተባበረች ኢትዮጵያን ገንብተን የማትከፋፈል ኢትዮጵያን ለትውል ማሳለፍ አለብን። ይህንን ምርጫ አይፈታውም ምክክር እንጂ።

 

2.    በቅርፀ መንግስት ጉዳይ

 

ቅርጸ መንግስት አንድ ፓርቲ ሲመጣ የሚገነባው ሌላው ሲመጣ የሚያፈርሰው አካል አይደለም። የሃገር ተክለ ሰውነት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርጸ መንግስት ላይ አያሌ ክርክር አለን። አሁን ባለው ቅርጸ መንግስትም ላይ ብዙ ጥያቄዎች ስለሚነሱ ምክክር ያስፈልጋል። ስርዓተ መንግስቱ ፓርላመንታሪ ይሁን ፕሬዝዳንታዊ፣ ወይስ የተዳቀለ? ወይስ ሌላ የተሻለ ቅርጸ መንግስት መፍጠር ይችላላ ወይ? የሚለው በምክክር ነው የሚፈታው። ስለ ቅርጸ መንግስት ስናወራ የምርጫ ስርዓታችንንም ይመለከታል። ተመጣጣኝ ውክልና ወይስ ፈርስት ፖስት ፖስት የሚባለውን ምርጫ አይነት እንከተል። የፌደሬሽን ምክር ቤት እንዴት ይዋቀር? በቀጥታ ምርጫ ወይስ በምልመላ? ወይስ በምርጫና ምልመላ፣ የህገ መንግስት ዳኛ ይኑረን ወይስ ሱፕሪም ኮርቱ ደርቦ ይስራው? ወይስ ሌላ ዘዴ አለ?  የፌደራል ስርዓቱን ውቅር በተመለከተ ምን እናድርግ? አሁን ያለው የፌደራል ስርዓት የዴሞክራሲ ክፍተቶች እንዴት ይስተካከላሉ? የርዕሰ ከተማ ወይም ከተማዎች አመራረጥን በሚመለከት ምን እናድርግ? የመሳሰሉትን ከቅርጸ መንግስት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በምርጫ አንፈታውም።  ይህንን ምርጫ ያሸነፈ አንድ ፓርቲ አይፈታውም። በምክክር የሚፈታ ነው።

 

3.    ብሄራዊ ማንነትንና የብሄር ማንነትን እንዴት እንንከባከብ

 

ይህ ጉዳይ ከፌደራል ስርዓቱ ጋር አብሮ የሚነሳ ቢሆንም ነገር ግን እንደ ማህበራዊ ጉዳያችን እነዚህን ማንነቶች አስታራቂ መርሆዎችን ማፍለቅ ግድ ይለናል። ይህንን መርሆ ምርጫ አያፈልቀውም። የግድ ምክክር አድርገን ተወያይተን ለሁለቱም ማንነቶች መሮጫ መሞችን ማስመርና ተቋማትን መገንባት ይገባናል። ይህንን ጉልህ ጉዳይ ምርጫ ሳይሆን ምክክር ነው የሚፈታው።

 

 

4.    ብሄራዊ ምልክቶች

 

ሌላው ምክክር የሚሻው ጉዳይ የምልክቶቻችን ጉዳይ ነው። ባንዲራችን፣ የሃገር ምልክት የሚሆኑን እሴቶች ጉዳይ፣ መዝሙሮቻችን ሁሉ በምክክር ነው የሚፈቱት። አንድ ፓርቲ አሸንፎ የሚፈጥረው መዝሙር ለሌላው ዘፈን ብቻ ነው።

 

5.    ያለፈ መጥፎ ትውስታዎች እንዴት ይታዩ

 

ሌላው ጉዳይ እሰከ ምክክራችን ዋዜማ ድረስ የደረሱ ጉልህ ግድፈቶች፣ በምክክር፣ በካሳ፣ በፍትህ የሚሽሩ ቁስሎች ሁሉ በምክክር ነው የሚፈቱት። ምርጫ አይፈታቸውም። የሽግግር ፍትህ ነው የሚፈታው። ከሃቀኛ ምክክር በዘገየን ቁጥር ስርዓት ያቆሰላቸው ዜጎች ሁሉ እድሚያቸው እየጨመረ ሳንደርስላቸው እየሞቱ ነው።

 

6.    የመሬት ላራሹ ጥያቄ

 

የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በአንድ ፓርቲ አሸናፊነት አይወሰንም። ፓርቲዎች በእርሻ ፖሊሲ ሊለያዩ ይችላሉ እንጂ በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ላይ አንድ አቋም እንደ ሃገር መያዝ አለብን። ይህንን ምርጫ አይፈታውም።

 

 

7.    ቋንቋና ተግባቦት

 

ብዝሃ ሃገር ስንሆን ወደ መቶ የሚጠጉ ቋንቋዎች አሉን። እነዚህን ቋንቋዎች በአግባቡ ለመጠቀም መርሆ መቅረጽ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ምክክር ይሻል። ምርጫ አይፈታውም።

እነዚህን ጉዳዮች አስቀድመን ሳንፈታ ወደ ምርጫ መሮጥ ሃገረ መንግስት ሳይረጋ እየረገበ እንዲኖር አድርጓል። በዚህ መሰረት በተለይ በዚህ ሰዓት በነዚህ ጉዳዮች ላይ ሃቀኛ ምክክር ለማድረግ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ማቋቋም አለብን። አንዱ የሽግግር መንግስትን ግድ የሚለው ይህ መሰረታዊ ጥያቄ ነው።

 

 

5.    የተዝለፈለፈ ምጣኔ ሃብትና ማህበራዊ ሃብት

 

የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት ሁኔታ በግለሰቦች የኑሮ ደረጃ ስንለካው በተለይ ሰራተኛው እጅግ ከባድ ድህነት ውስጥ ወድቋል። መንግስት ኢኮኖሚው እያንሰራራ ነው ኢዮጵያ እያደገች ነው ይላል። በተግባር የምናየው የህብረተሰቡ ኑሮ ደግሞ እጅግ አሳዛኝ ሆኖ ይታያል። የብራችን የመግዛት አቅም በዚህ መንግስት እጅግ ወድቋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተደረገ በተባለ ማግስት የሃገሪቱ እውነተኛ አጠቃላይ ምርት በግማሽ ወድቋል። በተከታታይ በፍጥነት እየገሸበ መጥቶ ዛሬ አንድ ዶላር 154. 64 ብር፣ አንድ የእንግሊዝ ፓውንድ 202.35 ብር አንድ ዩሮ  180 ብር   አንድ የቻይና  ዩን 21.46 ብር ገብቷል። ይህ የብር ግሽበት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የተከናወነ ሲሆን በዚህ ፍጥነት ገንዘባችን ሲደክም የህዝቡ የመግዛት አቅም ተመቷል። በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የብር ግሽበት (currency devaluation) መነሻ አንድ ሃገር ኤክስፖርት መር የሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ ከገባ ያንን በሃገር ውስጥ ያመረተውን ብዙ ምርት እየጠረገ ለመግዛትና ወደ ውጭ ለመላክ የሃገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን ስለሚያበረታታ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ነበር ይባላል። የእኛ ሃገር ግሽበት ግን ከዚህ የተቃረነ ነው። የንግድ ሚዛናችን በጣም በተዛባበት ዘመን፣ የሃገር ውስጥ ምርታችን በግጭት ምክንያት ዝቅ ባለበት ሰዓት ነው ይሄ ውሳኔ የተወሰነው። በዚህ የንግድ ክፍተት ላይ ሆነን ገንዘባችን ሲጋሽብ ትናንትና በአንድ ቢሊዮን ብር የገዛነውን ማዳበሪያ ዛሬ እስክ ስድስት ቢሊዮን ብር እንድናወጣበት ያደርገናል ማለት ነው። በነዳጅ፣ በመድሃኒት፣ በኢንዱስትሪ ግብዓቶች፣ በአልባሳት ወዘተ ሁሉ እጥፍ እጥፍ እንድንከፍል ስላደረገን ሃገሪቱን ለከፋ ችግር ዳርጓታል። ሃገራችን በከፍተኛ የሰላም እጦት ውስጥ ስትናጥ ስለቆየች የሚበቃትን ልታመርት አትችልም።

 

በተለይ ሰራተኛው የግሽበቱ ችግር ገፈት ቀማሽ በመሆኑና እጅግ በመጎሳቆሉ የኢትዮጵያ ቢሮክራሲም ሊፈርስ ነው። ሰራተኛው ተቋማቱን ሊያራምድ የሚችለው፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ማህበራዊ ተቋማት ሁሉ ሊያገለግሉ የሚችሉት ጤነኛና ትዳሩን ያሸነፈ ሰራተኛ ሲተውን ነው። ሰራተኛው በምጣኔ ሃብት ችግር ሲጎሳቆል ቢሮክራሲው ይዝለፈለፋል። ምጣኔ ሃብታችን መዋቅራዊ ችግሮች ውስጥ ስለገባና ፖለቲካል ምጣኔ ሃብታችን ስለተበላሸ እንዲህ በምርጫ የሚቀለበስ ችግር አይሆንም። አገሮች ሃይፐር ኢንፍሌሽን ውስጥ የሚገቡት ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ሲገጥማቸው ነው። ኢትዮጵያም ውስጥ የሚታየው ይሄ ነው።  ሃገሪቱ የግድ የጽሞና ጊዜ ወስዳ የሽግግር ጊዜ ወስዳ ፖለቲካዊ ችግሮቿን መፍታት አለባት አንዱ የሽግግር ጊዜ ገፊ ምክንያት ይሄ ነው። በዚህ የኑሮ ውድነት መሃል መንግስት ቢሮ ክራሲውን ሊነዳው አይችልም። አገረ መንግስትም ሊቀጥል አይችልም።

 

ጣሊያን በቅርብ አመታት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ገብታ ነበር። ይህቺ ሃገር ችግር ውስጥ ስትገባ የወሰደችው ርምጃ አንድ ነው። እሱም የሽግግር ጊዜ መፍጠር ነበር። በዚህ ምክንያት የቴክኖክራትስ  ጊዚያዊ መንግስት አቋቁማ ችግሩን ማቀብ መፍትሄ መፈለግ ችላለች ሃገሮች ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ሲገጥማቸው ወደ ሽግግር ያመራሉ። ሽግግር የፖለቲካ አንድ መፍትሄ ስለሆነ።

 

ከምጣኔ ሃብታችን ቀጥሎ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባው ሃብታችን ደግሞ ማንበራዊ ሃብታችን ነው። በጣም ቅራኔ የበዛበትና የብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ በቆየን ቁጥር ከህዝባችን መሃል መተማመን እየተነነ መጣ፣ ፍቅርና መረዳዳት፣ እምነትና ክብር እየተነነ መጣ። እነዚህን ሃብቶች ለመጠበቅ የፖለቲካ ለሂቃን እርቅ ወሳኝ ነው። ለዚህ ደግሞ የሽግግር ጊዜ እጅግ ወሳኝ ምዕራፍ ይሆናል። የሽግግር ጊዜ ውስጥ ስንገባና የፖለቲካ መፍትሄ መንገድ ስንጀምር ማገገሚያ የሚሆን ብድርና እርዳታ በሰፊው ማግኘት እንችላለን።

                                


ምርጫን እቃወማለሁ! አካታች የሽግግር መንግስት ይቋቋም

 

 

6.       ምርጫው ይዟቸው የሚመጡ ፈጣንና አዳሪ ግጭቶች

 

ገዢው ፓርቲ ብልጽግና በባሌም በቦሌም ብየ ይህንን ሰባተኛውን ምርጫ አካሂጄ የእውቅና ሰርተፍኬት ይዤ እቀጥላለሁ ብሎ ያስባል። ተላላ ፓርቲ......... ከፍ ሲል ስለምክክር ስናወራ ከምርጫ በፊት ምክክር ይቅደም የምንለው አንድም ምርጫ ይዟቸው የሚመጣ አሁናዊ ግጭቶችና አዳሪ ግጭቶች ስላሉብን ነው። በዚህ ገጽ ላይ በተለይ በምርጫው ጊዜ ግጭትን ሊያመጡ ከሚችሉ አካባቢዎች መካከል የወልቃይት፣ የራያን፣ ቦረና ውስጥ የተወሰኑ አካባቢዎችን ማንሳት እንችላለን። በዚህ ሰዓት የወልቃይት አስተዳደር በተለይ በትግራይና በአማራ አካባቢ ከፍተኛ የአስተዳደር ጥያቄ አስነስቶ ያለና ቁጭ ብሎ የፖለቲካ ድርድርን የሚጠይቅ አካባቢ ነው። አብይ አህመድ ስለ ወልቃይት ተጠይቆ ሲናገር አንድም በሪፈረንደም ሊፈታ ይችላል ሲል ተደምጧል። ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት እነዚህ አጨቃጫቂ ቦታዎች ከትግራይ ክልል ውጭ ሆነው ለተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ይደረግባቸው የሚል ውሳኔ አሳልፏል። በመጀመሪያ ደረጃ የፌደሪሽን ምክር ቤት ውሳኔ በጣም ቁንጽል ውሳኔ ነው። የዚህ አካባቢ ችግር የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ብቻ አይደለም። የማንነት፣ የወሰንና የአስተዳደር ጥያቄ ነው። ይህ ችግር ደግሞ በአጠቃላይ በፌደራል ስርዓቱ ክለሳ ጊዜ የሚታይ እንጂ በቁንጽል የሚፈታ ችግር አይደለም። ይህ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ግጭትን ከማምጣቱም ባሻገር የህግ ክፍተቱም በጣም ሰፊ ነው። ምርጫ ቦርድ ይህንን ውሳኔ ከማሳወቁ በፊት ወልቃይት በትግራይ ክልል ሆኖ ይካሄዳል ሲል ነበር። በአንድ የምርጫ ዘመን ሁለት የሚጋጩ ካርታዎችን እያመጣ ያንን አካባቢ ያተራምሳል። ይህ የሚያስተምረን አንድ ትልቅ ነገር አለ። አገሪቱ ምርጫ የማይፈታው ችግር አሉባት፣ ምክክር ይቅደም የምንለው ለዚህ ነው።  ዛሬ የምናየው የወልቃይት ችግር የስርዓታዊ ግጭቶቻችን ችግሮች ማሳያ ነው።

 

ዛሬ ምርጫ ቦርድ ይህንን ውሳኔ ሲያሳልፍ ትግራይ ክልል ተቃውሞ አሰምቷል። አብይ አህመድ ትግራይን ከዚህ በፊት ምርጫ ቦርድ የማያውቀው ምርጫ አድርገሻል ብሎ ጦርነት ከፍቷል። ዛሬ ደግሞ ሰባተኛውን ምርጫ አላደርግም ብለሻል ብሎ ጦርነት ሊከፍት ይመስላል። ሁላችን ኢትዮጵያውያን ልንቃወም ይገባል። የወልቃይት ችግር የሚፈታው በአጠቃላይ በፌደራል ስርዓቱ ክለሳ ማዕቀፍ ውስጥ ነው። የአዲአ አበባ፣ የድሬዳዋ፣ የሞያሌና የሌሎች አጨቃጫቂ ቦታዎች ችግር የሚፈታው በምክክር ነው። ለዚህ ደግሞ ሃቀኛ የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋል። አካታች የሽግግር ጊዜ ነው ወደ ሃቀኛ ምክክር የሚመራን።

 

ሌላው ጊዜ ጠብቆ የሚነሳው ግጭት ደግሞ ከማንነት ጋር የተያያዘው ምርጫ ነው። ለምሳሌ ድሬዳዋን በተመለከተ አብይ አህመድ ያነሳው የማንነት ጥያቄን  ምርጫ ላይ ያለውን ክፉ ጥላ ማሰብ ተገቢ ነው። ይህ ስጋት ያለው ህዝብ ማንነትን ፍለጋ ውስጥ ይገባል። ሃሳብን ሳይሆን ማንነትን ፈልጎ በሚሰጥ የምርጫ ቅራኔ ውስጥ ይገባል። ይህ ችግር  በቅድመ ምርጫም ይሁን በድህረ ምርጫ ወቅት ቅራኔን ያመጣል። ሁነኛ አስተዳደር ለመምረጥ ከፍተኛ ችግርም ነው። ቀድሞ በምክክር ተስማምቶ ድሬ የሁላችን ከተማ በሚል የተባበረ ስሜት ነው ምርጫ የሚሰምረው። በጥቅሉ ይህ ምርጫ ወዲያው ካሉበት ግጭቶች በተጨማሪ ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ሃገረ መንግስቱን ሲንጥ መክረሙ ከወዲሁ የሚታይ ነገር ነው። አንዱም ወደ ሽግግር መንግስት የሚመራን ገፊ ምክንያት ይሄ ነው።

                            


                    ምርጫን እቃወማለሁ! አካታች የሽግግር መንግስት ይቋቋም

 

 

 

7.    የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ እየተስፋፋ የመጣው የሰሜን ጦርነት ጉዳይ

 

ምርጫ ቦርድ በቅርቡ አንድ ጥናት አድርጊያለሁ ብሎ መግለጫ ሰጠ። ጥናቱ ያነጣጠረው በሃገሪቱ ውስጥ ከጸጥታ አንጻር ምርጫን ለማካሄድ ያለውን አስቻይ ሁኔታ የሚመለከት ግምገማ እንደነበረ ተገልጿል። በዚሁ መሰረት የሃገሪቱን የጸጥታ ሁኔታ በሶስት ቀለማት ማለትም አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ብሎ ደልድሎታል። ይሁን እንጂ ይህንን የሰራውን ጥናት በግልጽ ለኢትዮጵያ ህዝብ አላካፈለም። በድረ ገጹም ላይ አላካፈለም። ይሄ ትልቅ ጥያቄ ያስነሳል። የሆነ ሆኖ ምርጫ ቦርድ እንደሚለው አረንጓዴው ላይ በሰላም ምርጫ ማካሄድ የምንችል ሲሆን ቢጫው አካባቢ ከጥንቃቄ ጋር ምርጫ ማድረግ ይቻላል ቀይ የተቀለሙት ወረዳዎች ላይ ግን ምርጫ ማካሄድ አይቻልም የሚል ነው። በርግጥ ከፍ ሲል እንዳነሳነው ይህ ጥናት በመቶኛ እየተገለጸ ቢነገር ተገቢ ነበር። ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ይህንን መረጃ ለራሱ ብቻ ደብቋል። ከሁሉም በለይ ግን በተለይም በቢጫ ከባቢ ውስጥ ማለትም ሙሉ በሙሉ ሰላም የማይሰማቸው አካባቢዎች ውስጥ ምርጫ ከጥንቃቄ ጋር እናደርጋለን የሚለው ግምገማው ግን በጣም ሃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ነው። የምርጫ ሂደት ከባድ ሰላም እና ዋስትናን ይጠይቃል። ምርጫ እኮ የአንድ ቀን ተግባር አይደለም። የምርጫ ዘመቻ ይኖራል፣ ትላልቅ ድምፅ ሰጪው ህዝብ ወደ መመዝገቢያ ጣቢያዎች ሄዶ ይመዘገባል፣ ዕጩ ተወዳዳሪዎችም ለምርጫ ይመዘገባሉ፣ ስብሰባዎች ይኖራሉ፣ እጩዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ምረጡን ይላሉ፣ ውይይትና ክርክር ይደረጋል የሞቁ የሃሳብ ግጭቶች ስሜት እያየለባቸው የተለያዩ ግጭቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህ ሁሉ ከባድ የፖለቲካ ስራ በቢጫ ወይምከማስጠንቀቂያ ጋር.....” ተብሎ ሊፈጸም አይችልም። ማስጠንቀቂያ በሚጠይቅ ከባቢ ስር ምርጫ ይደረጋል የሚለው የምርጫ ቦርድ ግምገማ ከፍ ሲል እንደገለጽኩት እንደምን ከምርጫ አፈጻጸምና ጽንሰ ሃሳብ ጋር የተፋለሰ ነው? ምርጫ ቦርድ በደፈናው አረንጓዴ፣ቢጫና ቀይ እያለ የሚያምታታ መግለጫ ከማውጣት፣ ቢጫና ቀይ ቀለሞች ወደ አረንጓዴ ሳይቀየሩ ምርጫ ማስፈጸም አልችልም ብሎ ለፓርላማው ማሳወቅ ነበረበት። ተቋም ነጻ ሲሆን ይህንን ያደርጋል።

 

ከፍ ሲል ከጸጥታ አንጻር የምርጫ ቦርድን መነሻ አድርገን ጀመርን እንጂ የሃገሪቱ ጸጥታ ሁኔታ ከደፈረሰ ቆየ አይደለም ወይ? እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ለመሆኑ የትኛው አካባቢ ነው አረንጓዴ ቀለም የሚሸለመው? ሃገሪቱ አብዛኛው አካሏ በትጥቅ ትግል ድባብ ውስጥ ባለበት ሰዓት ሌላው አካባቢ ሰላም ነው ማለትስ ይቻላል ወይ? አማራ ክልል፣ ትግራይ ክልል፣ ኦሮምያ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል በተለይ በከባድ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የታወኩ አካባቢዎች ናቸው። አዲስ አበባ ዙሪያ ቱሉዲምቱ፣ ሰበታ አካባቢ የጸጥታ ስጋት የለም ወይ? ድንገት የሚፈጸሙ ወታደራዊ ጥቃቶች አሉ አይደለም ወይ? ብዙ ኤምባሲዎች ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከባድ ማስጠንቀቂያዎች ይሰጡ የለምን? ዛሬ ዜጎች ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ሞያሌ፣ ወደ ጎንደር፣ ወደ ደሴ፣ ወደ ጅማ፣ ወደ መቀሌ እንዳሻቸው ወጥተው መግባት ይችላሉ ወይ? መንግስት የጸጥታ ቁጥጥሩ ከጁ ከወጣ ውሎ አድሮ የለም ወይ? አማራ ክልል 47 በመቶ የሚሆኑ ልጆች ትምህርት ማቋረጣቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ዘግቧል። በሽህ የሚቆጠር ትምህርት ቤት በተዘጋበት ክልል ውስጥ እንዴት ነው ምርጫ ጣቢያ የሚከፈተው? ትግራይ ክልል ወደ ምርጫ እንደማይገባ የታወቀ ነው። ከፍ ሲል እንዳነሳነው የፕሪቶሪያው ስምምነት እያደገ መጥቶ ትግራይ ከፌደራሉ ጋር ያላትን ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ አግኝታለት መደበኛ ወደ ሆነ የፌደራልና የክልል መንግስት ግንኙነት ከተመለሰ በኋላ ወደ ምርጫ መግባት ይቻል ነበር። ነገር ግን በፌደራል መንግስትና በትግራይ መካከል ያለው የፖለቲካ ልዩነት እየሰፋ መጥቶ አልፎ አልፎም መንግስት ክልሉን በድሮን ሲጎበኝ ነው የሚታየው። ትግራይ በዚህ ሁኔት በምርጫ ውስጥ አለመግባቷ እንዴት ነው በሃገራዊ ምርጫው ላይ እንቅፋት የማይፈጥረው? አማራ ክልል የታችኛው የመንግስት መዋቅር ፈርሷል ማለት ይቻላል። ቀበሌዎችና ትናንሽ ከተሞች በፋኖ ጉብኝትና ቁጥጥር ውስጥ ናቸው። መካከለኛ ከተሞች ደግሞ ከፋኖ ራዳር ውጪ አይደሉም። በምርጫው ቀን ገባ ብለው ምርጫውን አስተጓጉለው መውጣት ለነሱ በጣም ቀላል ነገር ነው። ወደ ኦሮምያ ስንመጣ በየትኛውም የኦሮምያ አካባቢ ኦላ ምርጫን ማጥቃት አይሳነውም። የምርጫ ኮሮጆዎችን ይዘው የሚጓዙትን መጠየቅ፣ ምርጫ ማስተጓጎል ቀላል ነው። ጋምቤላ ውስጥ ከሁሉም የከፋ የጸጥታ ችግር አለ። የናት ንቅናቄ ደጋፊ ነን የሚሉ ሃይሎች ክልሉን የብጥብጥ ማዕከል አድርገውታል። በዚህ ክልል ምርጫ ጥሩ የብጥብጥ አውድ ከመፍጠር ወይም በእሳት ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ ያለፈ ሚና አይኖረውም። እንዴውም ምርጫ በጋምቤል ውስጥ ከፍተኛ ግጭትን ደቅኗል። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ስምንት መቶ ወረዳዎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ ስንቶቹ ናቸው ግጭት እያሰለሰ የማይጎበኛቸው? በየካቲት 17 የእንግሊዝ መንግስት ጥናት አጥንቶ የሚከተለውን ካርታ ነድፎ ለተጓዥ ዜጎቹ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። ይህ ካርታ የሚያሳየው  የሃገሪቱ አጠቃላይ የሰላም የጸጥታ ችግር ከባድ መሆኑን ነው።  አገር እንዲህ ሲሆን ስለሽግግር ያስባል፣ ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስባል እንጂ እንዴት የምርጫ ድግስ ይደግሳል?

ከዚህ በተጨማሪ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው በኢትዮጵያና በኤርትራ በኩል የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመ ነው። ይህ ጉዳይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም በዚህ ምርጫ ላይ ሌላ ተጽዕኖ ያመጣል ብቻ ሳይሆን ምን አልባትም ሃገረ መንግስቱን የሚያፈርስ ክስተትን ይዞ ሊመጣ ይችላል። አብይ አህመድ ከህወሃትም ከኤርትራም እዋጋለሁ ባይ ነው። ይህ ጦርነት በርግጥ ብዙ መዘዞችን ይዞ ሊመጣ ይችላል። አገረ መንግስቱን የሚፈታተን ይሆናል። በዚህ ቀውጢ ወቅት በአንድ በኩል ጦርነቱን እያካሄድኩ በሌላ በኩል ምርጫ አደርጋለሁ የሚል የሰከረ መንግስት ሲገጥም የኢትዮጵያ ህዝብ አብይ አህመድ ከስልጣን ይውረድ አካታች የሽግግር መንግስት ይቋቋም ማለት አለበት  አሁን የተበላሸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ዲፕሎማሲያችን ቀና የሚለው የፖለቲካ ለውጥ ስናደርግ ብቻ ነው። ይህንን ጦርነት እያወገዝን ኢትዮጵያ ውስጥ ሽግግርን ማቀንቀን ይገባናል።

 

ምንጭ  Regional risks - Ethiopia travel advice - GOV.UK

 


ምርጫን እቃወማለሁ! አካታች የሽግግር መንግስት ይቋቋም






8.    የተፈናቃዮች ጉዳይ

 

የአገር ውስጥ መፈናቀል ጉዳይ ሲነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአራት ሚሊዩን በላይ የሆኑ  ወገኖቻችን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። መፈናቀል በኢትዮጵያ የማያባራ ክስተት ሆኗል። አንድ ህዝብ ከሁለት ጊዜ በላይ የሚፈናቀልበት ሁኔታም ተመዝግቧል። ታዲያ ሃገሪቱ ሰባተኛ የምርጫ ድግስ ደግሻለሁ ስትል እነዚህን ወገኖች ከቶ ምን ልታደርጋቸው ነው? በየድንኳኑ ሄደን በተፈናቀላችሁበት ቦታ ላይ አንድ ሊቀመንበር ምረጡ ብለን ልንሳለቅባቸው ነው? ወይስ ለዚያው ለድንኳን ህይወታቸው አስተባባሪ ምረጡ ነው የምንላቸው? ይህ ጉዳይስ በታሪክ አያስጠይቀንም ወይ? ነው ወይስ ይህንን ሁሉ ህዝብ ጥለነው ምርጫ ልናደርግ ነው?  ይህንን ጽሁፍ ሳዘጋጅ ሳልሳይ ወያኔ ተፈናቃዮችን ምረጡ የሚለውን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ እቃወማለሁ ብሏል። በርግጥ ምርጫ ቦርድ እነዚህን ዜጎች የሚሳለቅባቸው ይመስላል። ከወለጋ ተፈናቅለው አምስት አመት በደብረ ብርሃን ድንኳን ውስጥ ያሉን ዜጎች ነው ለዚያ ለተፈናቀላችሁበት ቀበሌ የህዝብ ተወካይ ምረጡ የሚላቸው? ግፍ ነው በእውነት አራት ሚሊዩን ህዝብ ማለት እኮ ከጅቡቲ ህዝብ ይበልጣል፣ ከኤርትራ ህዝብ ይበልጣል፣ ካስዋዚላንድ፣ ከሞሪሽየስ.... ከብዙ ብዙ ሃገራት ህዝብ ይበልጣል። እንዴት ነው ይህንን ህዝብ በድንኳን ላይ ጥለን የፖለቲካ መፍትሄ ሳንፈልግ በድንኳንህ ምረጥ የምንለው?  የሽግግር መንግስት ይቋቋም!

Over 4 million displaced in Ethiopia, says UN migration body | Arab News PK

Source AFP

 


ምርጫን እቃወማለሁ! አካታች የሽግግር መንግስት ይቋቋም

 

 


 

9.    የሃገረ መንግስት በቋፍነት

 

 

ፓርቲዎች ቢፈርሱ በአገር ይጠገናሉ። ቡድኖች ቢቆስሉ በአገር ይጠገናሉ። ግለሰብ ቢጎዳ በአገር ይካሳል። አገር ከፈረሰ ግን ወዴት ይደረሳል? አገረ መንግስት ሁል ጊዜም በከፍታም በዝቅታም መኖር አለበት ይሁን እንጂ ብዙ ዱላና ምት የበዘባት በከፍተኛ ማዕበል የተመታ አገረ መንግስት ለአጭር ጊዜ ወይም ለረጅም ጊዜ አለያም እስከ ሃቹ የመፍረስ አደጋ ይኖረዋል። ሶማሊያ ውስጥ አገረ መንግስት ፈርሶ አያሌ አመታት የሱማሌ ህዝብ መከራውን አየ። የሶማሌ መንግስት እያዘመመ ሲመጣና አገረ መንግስቱ በቋፍ ሲሆን ዚያድባሬ የፖለቲካ መፍትሄ መስጠት አልቻሉም። ስልጣን ወይም ሞት ብለው አጥፍተው ጠፉ። አንድ ሃገር በከፍተኛ የፖለቲካ ተቃርኖ ውስጥ ሲገባና አገረ መንግስቱ እገጭ እጓ ሲል በፍጥነት የአደጋ ጊዜ መብራት ማሳየትና የአደጋ ጊዜ መንግስት መፍጠር አገር ያተርፋል። በቋፍ ላይ ያለ ሃገረ መንግስት በምርጫ እንዴት ሊተርፍ ይችላል? ምርጫ እንዴውም በከፍተኛ ሁኔታ እምቅ ግጭቶችን ይዞ የሚመጣ ክስተት ነው የሚሆነው።

የአለም ሃገራትን ሃገረ መንግስት ቁመና በየ ዓመቱ የሚለካ አንድ ተቋም አለ። ፈንድ ፎር ፒስ ይባላል። ይህ ተቋም በዚህ አመት ለኢትዮጵያ የሰጠው ነጥብ እጅግ አሳሳቢ ነው። ከአምናው ዘንድሮ ነጌቲቭ ውስጥ ነው የገባችው። የሚያፈርሳችሁ ነገር በዝቷልና ከባድ ጥንቃቄ ያስፈልጋችኋል ከተባሉት 15 አገራት አንዷ ናት ኢትዮጵያ። እንዲህ አይነት ችግር ሲገጥም ምርጫ አይደለም ችግሩን የሚፈታውና አገረ መንግስቱን የሚታደገው። በዚህ ጊዜ ብሄራዊ መግባባትና የሃይል መካፈል ዘዴ ነው አገረ መንግስቱን የሚያረጋው። በዚህ ፈንድ ፎር ፒስ ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ በለሂቅ ክፍፍል ከአስሩ ስምንትና ዘጠኝ ነው የምታስመዘግበው። ከአስሩ አስር ያገኘ ሃገር ለሂቁ ሙሉ በሙሉ የተከፋፈለበት የወደቀ አገር ማለት ሲሆን ዘጠኝና ስምንት ነጥብም ወደ መጨረሻው የተጠጋ ነጥብ ነው። በርግጥ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደምንታዘበው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተቃዋሚው ጎራ ያለው ክፍፍል እየጠበበ ቢመጣም ከመንግስት ጋር ያለው ልዩነት ግን በጣም እየሰፋ መጥቷል። ታዲያ በዚህ ለኢትዮጵያ ከባድ ጊዜ ህልውናዋን የሚታደገው አዳኝ መንገድ ምርጫ ሳይሆን ወደ ሽግግር ማምራት ብቻ ነው።

 

 

 


ምርጫን እቃወማለሁ! አካታች የሽግግር መንግስት ይቋቋም

                     





                                አያዎ (ፓራዶክስ)  እን መደምደሚያ

 

 

የአብይ መንግስት በከፍተኛ አያዎ ውስጥ ይገኛል። የአሰብ ወደብ የእኔ ነው ለዚህ የሚከፈለውን መስዋዕትነት እከፍላለሁ ይልና በሌላ በኩል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ኤርትራን ምከሩልን ድንበር ታክብር የአልጀርሱ ስምምነት ይከበር ይላል። አሰብ የእኔ ነው የሚል መንግስት ቢያንስ የአልጀርሱን ስምምነት በፓርላማ እንደገና ውድቅ ያደርጋል። አንካራ ላይ የጎረቤት አገር ድንበር አከብራለሁ ብሎ ይፈርምና ኤደን ባህረ ሰላጤ የሁላችን ነው ይላል። እርዳታና ብድር እየለመነ የአለም አንደኛ ቤተ መንግስት ይሰራል። ራበኝ ላለ ሰው መዝናኛ ያሳያል። ሰራተኛው ረሃብ ላይ ነው ሲባል አገር እያንሰራራች ነው ይላል። በጦርነትና በግጭት መሃል የምርጫ ድግስ ይደግሳል። ተቃዋሚውን አግልሎ፣ ለሂቁን ሁሉ አግልሎ በሃገረ መንግስቱ ላይ ያለው ቅራኔ በምክክር ሊፈታ ጉባኤ ሊካሄድ ነው፣ ኢትዮጵያ እየመከረች ነው ይላል። ቁልቁል እየነዳ ሽቅብ እያቀናን ነው ይላል። የድሃውን ቁጥር ጨምሮ እንደ ስሜ ብልጽግና አይሸታችሁም ወይ አፍንጫ የላችሁም ወይ? ይላል። መደመር መመሪያዬ ነው እያለ በመቀነስ ሂሳብ ይመራል......... ይህ አያዎ ወይም ፓራዶክስ የጤነንት አይደለም። ብልጽግና እንደ ድርጅት ከፍተኛ የስነ ልቡና ቀውስ ውስጥ ነው የምንለው ለዚህ ነው። እንዲህ አይነት ቅራኔዎች በቀጠሉ ቁጥር አገር በሃይል ይጎዳል። ስለዚህ ነው ከፍ ሲል ወደ ሽግግር እናምራ ብለን የተማጸንነው።

 

ኢትዮጵያውያን ተባብረን ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ጊዜ መፍጠር አለብን። ይህ የሽግግር ምክር ቤት ምሁራንን፣ የፖለቲካ ሃይሎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ ሲቪክ ድርጅቶችን፣ የታጠቁ ሃይሎችን፣ ዲያስፖራውን ሁሉ ያካተተ መሆን አለበት። ይህ ምክር ቤት በዋናነት ሊኖሩት የሚገባው ተቋማት አንደኛ የምክክር ኮሚሽን፣ ሁለተኛ የሽግግር ፍትህ ኮሚሽን፣ ሶስተኛ የህገ መንግስት ክለሳ ኮሚሽን (constitution Revision Commission) እና የወትሮውን የመንግስት ቢሮክራሲ ስራ የሚሰራበት አደረጃጀት ናቸው። እዚህ ላይ የተሳካ ጅማሮ ካሳየን ኢትዮጵያ በርግጥ ተስፋ ያላት ሃገር ናት ።

 

          እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ ይጠብቅ

Geletaw Zeleke's New Book *** ETHIOPIAN POLITICS የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ይህ መጽሀፍ የማንነት ፖለቲካ እንዴትና ከየት እንደተነሳና ያለውን ችግሮች በዝርዝር ያስረዳል:: ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማህበረሰባዊ ግንኙነቶች ፈራርሰዋል። ደራሲው የሃገራችን መሰረታዊ ችግር የማህበረ ፖለቲካ ነው ይላል። ...